am_ulb/22-SNG.usfm

297 lines
25 KiB
Plaintext

\id SNG
\ide UTF-8
\h መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን
\toc1 መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን
\toc2 መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን
\toc3 sng
\mt መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን
\s5
\c 1
\p
\v 1 ከመዝሙሮች የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር። ልጃገረዲቱ ፍቅረኛዋን እንዲህ ትለዋለች፥
\v 2 ኦ በአፍህ መሳም በሳምከኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይሻላልና።
\v 3 ሽቶህ አስደሳች መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስ ሽቶ ነው፥ ስለዚህ ልጃገረዶች ወደዱህ።
\v 4 ካንተ ጋር ውሰደኝ፥ አብረንም እንሮጣለን። ሴቲቱ ለራሷ ትናገራለች፥ ንጉሡ ወደ ቤቱ ውስጥ አስገባኝ። ሴቲቱ ፍቅረኛዋን እንዲህ ስትል ትናገረዋለች፥ ደስ ብሎኛል፤ ስለ አንተ ደስ ይለኛል፤ በፍቅርህ ሐሴት ላድርግ፤ እርሱ ከወይን ጠጅ ይሻላል። ሌሎቹ ሴቶች ቢያደንቁህ ተፈጥሮአዊ ነው
\s5
\v 5 አንደኛዋ ሴት ለሌላይቱ ስትናገር፥ እኔ ጥቁር ነኝ፥ ቢሆንም ውብ ነኝ፥ እናንተ ከኢየሩሳሌም ወንዶች የተወለዳችሁ ሴቶች ልጆች፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች ጥቁር፥ እንደ ሰለሞንም መጋረጃዎች ውብ ነኝ።
\v 6 ጥቁር ስለ ሆንኩ ትኩር ብላችሁ አትመልከቱኝ፥ ምክንያቱም ፀሐይ አጥቁሮኛል። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቆጡኝ፥ የወይን አትክልት ጠባቂም አደረጉኝ፥ የራሴን የወይን ቦታ ግን አልጠበቅሁም። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
\s5
\v 7 ንገረኝ የምወድህ፥ መንጋህን የምታሰማራው የት ነው? በቀትር ጊዜስ መንጋህን የምታሳርፈው የት ነው? ከባልንጀሮችህ መንጋ ኋላ እንደሚቅበዘበዝ ሰው ለምን እሆናለሁ? ፍቅረኛዋ ሲመልስላት፥
\s5
\v 8 ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተዋብሽው ሆይ፥ አታውቂ እንደሆነ፥ የመንጋዬን ኮቴ ተከተይ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ።
\s5
\v 9 የኔ ፍቅር፥ በፈርዖን የሰረገላ ፈረሶች መካከል ካለችው ባዝራ ጋር አመሳሰልሁሽ።
\v 10 ጉንጮችሽ በማስዋቢያ ተውበዋል፥ አንገትሽም በዕንቁ ሐብል።
\v 11 የብር ፈርጥ ያለበት የወርቅ ማጌጫ እሠራልሻለሁ። ሴቲቱ ለራስዋ ስትናገር፥
\s5
\v 12 ንጉሥ ማዕዱ ላይ እያለ፥ የናርዶስ ሽቶዬ መዓዛውን ናኘው።
\v 13 ውዴ ለእኔ ልክ ሌሊቱን ሙሉ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
\v 14 ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ የወይን ቦታ ውስጥ እንደ ሂና የአበባ ዕቅፍ ነው። ፍቅረኛዋ ሲናገራት፥
\s5
\v 15 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ አንቺ ውብ ነሽ፤ እነሆ ያማርሽ ነሽ፤ ዓይኖችሽ እርግቦችን ይመስላሉ። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
\s5
\v 16 ውዴ ሆይ፥ እነሆ አንተ መልከ መልካም ነህ፥ ያማርክም ነህ። የለመለመው ሣር እንደ አልጋ ያገለግለናል።
\v 17 የቤታችን የማዕዘን ተሸካሚ የዝግባ እንጨት፥ የጣሪያችን ማዋቀሪያም የጥድ እንጨት ነው።
\s5
\c 2
\p
\v 1 እኔ በሜዳ የሚገኝ አበባ፥ በሸለቆም የሚገኝ አበባ ብቻ ነኝ። ሰውየው ሲናገራት፥
\v 2 ውዴ ሆይ፥ አበባ በእሾህ መካከል እንደሆነ አንቺም በሀገሬ ሴቶች ልጆች መካከል ነሽ። ሴቲቱ ለራስዋ ስትናገር፥
\s5
\v 3 በዱር ዛፍ መካከል እንዳለ የእንኮይ ዛፍ የእኔም ውድ በጎልማሶች መካከል ነው። በታላቅ ደስታ ከጥላው ሥር ተቀመጥኩ፥ የፍሬውም ጣዕም ጣፋጭ ነው።
\v 4 ወደ ግብዣው አዳራሽ አመጣኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ሰንደቁ ፍቅር ነው። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
\s5
\v 5 በዘቢብ ጥፍጥፍ ነፍስ ዝሩብኝ፥ በእንኮይ ጭማቂም አበርቱኝ፥ በፍቅር ተይዤ ደክሜአለሁና። ሴቲቱ ለራስዋ ስትናገር፥
\v 6 ግራ እጁ ከአንገቴ ሥር ነው፥ ቀኝ እጁም ያቅፈኛል። ሴቲቱ ለሌላዋ ሴት ስትናገር፥
\s5
\v 7 የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች፥ በፍቅር ግንኙነታችን ወቅት እስክንረካ ድረስ ላታቋርጡን በሜዳ ፍየሎችና በአጋዘኖች ቃል እንድትገቡልኝ እፈልጋለሁ። ሴቲቱ ለራሷ ትናገራለች፥
\s5
\v 8 የውዴ ድምጽ ነው! ኦ፥ በተራራዎች ላይ እየዘለለ፥ በኮረብታዎች ላይ እየተስፈነጠረ ሲመጣ ይታወቀኛል።
\v 9 ውዴ የሜዳን ፍየል ወይም ግልገል አጋዘንን ይመስላል፤ እነሆ እርሱ ከቤታችን ግድግዳ በስተኋላ ቆሟል፥ በመስኮቱ በኩል አተኩሮ፥ በፍርግርጉም አጮልቆ ይመለከታል።
\s5
\v 10 ውዴ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ "ውዴ ሆይ ተነሽ፤ የኔዋ ቆንጆ ከእኔ ጋር ነይ።
\v 11 ተመልከች፥ ክረምቱ አልፏል፥ ዝናቡም ቆሟል፥ ሄዷልም።
\s5
\v 12 አበቦች በምድር ላይ ታይተዋል፤ ወይን የሚገረዝበትና የወፎች ዝማሬ ጊዜ ደርሶአል፥ የእርግቦችም ድምጽ በምድራችን ተሰምቷል።
\v 13 የበለስ ዛፍ አረንጓዴ ፍሬዎቿ በስለዋል፥ ወይኖቹም አብበዋል፥ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል። ውዴ ሆይ ተነሽ፥ የኔዋ ቆንጆ ነይ።
\s5
\v 14 በዐለት ሥንጣቂ ውስጥ፥ በድብቁ የተራራማው ቋጢኝ ስንጣቂ ውስጥ ያለሽ እርግቤ ሆይ፥ ፊትሽን ልየው። ድምጽሽን ልስማው፥ ድምጽሽ ጣፋጭ ነውና ፊትሽም ውብ ነው።" ሴቲቱ ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 15 የወይናችን ቦታ አብቦአልና የወይን ቦታዎችን የሚያበላሹትን ትናንሽ ቀበሮዎች ያዙልን።
\s5
\v 16 ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ እርሱ መንጋውን በአበቦቹ መካከል በደስታ ያሰማራል።
\v 17 ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥ ውዴ ሆይ፥ ተመለስ፣ የንጋቱ ቀዝቃዛ ንፋስ ሳይነፍስ፥ ጥላውም ሳይሸሽ። ተመለስ፤ በጎርበጥባጣዎቹ ኮረብቶች ላይ የሜዳ ፍየልን ወይም ግልገል አጋዘንን ምሰል።
\s5
\c 3
\p
\v 1 ሌሊት በመኝታዬ የምወደውን ናፈቅሁት፤ ፈለግሁት፥ ነገር ግን ላገኘው አልቻልኩም።
\v 2 እኔም ለራሴ፥ "እነሣለሁ፥ ወደ ከተማው ውስጥ፥ ወደ ጎዳናዎቹና ወደ አደባባዮቹ እሄዳለሁ፤ ውዴንም እፈልገዋለሁ" አልኩ። ፈለግሁት፥ ላገኘው ግን አልቻልኩም።
\s5
\v 3 ጠባቂዎች በከተማው ውስጥ ለጥበቃ ሲዘዋወሩ አገኙኝ። እኔም፥ "ውዴን አይታችሁታል?" ብዬ ጠየቅኋቸው።
\v 4 ከእነርሱ ጥቂት እልፍ እንዳልኩኝ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት። ያዝኩት፥ ወደ እናቴ ቤት፥ ወደ ፀነሰችኝም መኝታ ቤት እስካመጣው ድረስ አልለቀውም። ሴቲቱ ለሌላይቱ ሴት ስትናገር፥
\s5
\v 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ሰዎች ሴቶች ልጆች፥ በፍቅር ግንኙነታችን እስክንረካ ድረስ ላታቋርጡን በሜዳ ፍየሎችና አጋዘኖች እንድትምሉልኝ እፈልጋለሁ። ወጣቷ ሴት ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 6 ይህቺ በዕጣንና ከርቤ፥ ነጋዴዎችም በሚሸጡት ልዩ ልዩ ቅመም በተቀመመ ሽቶ ተቀብታ እንደ ጢስ ምሶሶ ከምድረ በዳ የምትወጣ ማናት?
\v 7 እነሆ እርሱ የሰለሞን ተንቀሳቃሽ አልጋ ነው፤ ስልሳ የእስራኤል ወታደሮች፥ ስልሳ ጦረኞች ከብበውታል።
\s5
\v 8 እነርሱ በሰይፍ የላቁ ናቸው፥ በጦርነትም የታወቁ። እያንዳንዱ በወገቡ ሰይፍ አለው፥ በሌሊት የሚያሸብሩትን ለመከላከል ታጥቀዋል።
\v 9 ንጉሥ ሰለሞን ከሊባኖስ በመጣ እንጨት ሰው ተቀምጦበት የሚሸከሙትን [ለአንድ ሰው መቀመጫ የሚሆን ወንበር የሚይዝ] ሳጥን ለራሱ ሠራ።
\s5
\v 10 ምሶሶዎቹን ከብር፥ ጀርባው ከወርቅ፥ መቀመጫው ከሐምራዊ ጨርቅ ተደርጎ ተሠራ። ውስጡ የተዋበው በኢየሩሳሌም ሰዎች ሴቶች ልጆች ነበር። ወጣቷ ለኢየሩሳሌም ሴቶች ስትናገር፥
\v 11 የጽዮን ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ሂዱ ውጡ፥ ንጉሥ ሰለሞንን ትኩር ብላችሁ እዩት፥ በሕይወቱ በተደሰተባት በዚያች ቀን፥ በሠርጉ ቀን እናቱ የደፋችለትን አክሊል ጭኖ።
\s5
\c 4
\p
\v 1 ኦ፥ ወዳጄ ሆይ፥ አንቺ ውብ ነሽ፥ እነሆም ቆንጆ ነሽ። በመሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እርግቦች ናቸው። ጸጉርሽ ከገለዓድ ተራራ ቁልቁል የሚወርደውን የፍየል መንጋ ይመስላል።
\s5
\v 2 ጥርስሽ በቅርቡ ተሸልቶ ከመታጠቢያው ሥፍራ የሚወጣውን የበግ መንጋ ይመስላል። እያንዳንዱ መንታ ወልዷል፥ በመካከላቸውም መካን የለም።
\s5
\v 3 ከንፈሮችሽ ቀይ የሐር ፈትል ይመስላሉ፤ አፍሽ ውብ ነው። ጉንጮችሽ በመሸፈኛሽ ውስጥ ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላል።
\s5
\v 4 አንገትሽ በረድፍ በተደረደሩ ድንጋዮች ላይ የተገነባውን የዳዊትን የጥበቃ ማማ ይመስላል፥ አንድ ሺህ ጋሻ፥ የወታደሮቹ ሁሉ ጋሻ በእርሱ ላይ ተሰቅሏል።
\v 5 ሁለቱ ጡቶችሽ በአበቦች መካከል የተሰማሩ ሁለት የአጋዘን ግልገሎችን፥ መንታም የተወለዱ የሜዳ ፍየሎችን ይመስላሉ።
\s5
\v 6 ጎሕ እስኪቀድና ጥላው እስኪሸሽ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ፥ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ።
\v 7 ውዴ ሆይ፥ ሁለመናሽ ውብ ነው፥ እንከንም የለብሽም።
\s5
\v 8 ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ። አዎን፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፥ ከአማና ጫፍ፥ ከሳኔርና ከኤርሞን ጫፍ፥ ከአንበሶች ዋሻ፥ የነብሮች ዋሻ ከሆነውም ተራራ ነይ።
\s5
\v 9 እህቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ልቤን ሰርቀሽዋል፤ በአንድ አፍታ ዕይታሽ ብቻ፥ በአንድ ሐብልሽ ብቻ ልቤን ሰርቀሽዋል።
\s5
\v 10 እህቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት ያማረ ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ ምንኛ ይሻላል፥ የሽቶሽ መዓዛም ከቅመሞች ሁሉ።
\v 11 ሙሽራዬ ሆይ፥ ከንፈሮችሽ ማር ያንጠባጥባሉ፥ ማርና ወተት ምላስሽ ሥር ናቸው። የልብሶችሽ መዓዛ የሊባኖስን መዓዛ ይመስላል።
\s5
\v 12 እህቴ ሙሽራዬ የተቆለፈበት የመናፈሻ ቦታ ናት፥ የተቆለፈበት የመናፈሻ ቦታ፥ የታተመበትም ምንጭ።
\v 13 ቅርንጫፎችሽ የሮማን ዛፍ ከተመረጠ ፍሬ ጋር፥ ሂናና የናርዶስ ተክል፥
\v 14 ናርዶስና ቀጋ፥ ጠጅ ሣርና ቀረፋ ከልዩ ልዩ ቅመሞች ጋር፥ ከርቤና እሬት ምርጥ ከሆኑት ቅመሞች ሁሉ ጋር አሉባቸው።
\s5
\v 15 አንቺ የአትክልት ሥፍራ ምንጭ፥ የንጹህ ውሃ ጉድጓድ፥ ከሊባኖስ ወደ ታች የሚወርድ ምንጭ ነሽ። ወጣቷ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
\v 16 የሰሜን ንፋስ ሆይ ንቃ፤ የደቡቡም ንፋስ ና፤ ቅመሞቹ መዓዛቸውን እንዲሰጡ በአትክልት ሥፍራዬ ላይ ንፈስ። ውዴ ወደ አትክልቱ ሥፍራ ይምጣ፥ ከምርጡም ፍሬ ጥቂት ይብላ።
\s5
\c 5
\p
\v 1 እህቴ፥ ሙሽራዬ፥ ወደ አትክልቴ ቦታ መጣሁ፤ ከርቤዬን ከቅመሜ ጋር ሰብስቤአለሁ። የማር እንጀራዬን ከወለላው ጋር በልቻለሁ፤ ወይኔን ከወተቴ ጋር ጠጥቻለሁ። ጓደኞች ለአፍቃሪዎች ሲናገሩ፥ ጓደኞቻችን ሆይ ብሉ፤ ጠጡ፥ በፍቅርም ስከሩ። ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 2 እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን በሕልም ነቅቷል። የውዴ ድምጽ ነው፥ በሩን ያንኳኳል፥ "እህቴ፥ ውዴ፥ እርግቤ፥ እንከን የሌለብሽ ሆይ፥ ራሴ በጤዛ ርሷል ፀጉሬም በሌሊቱ እርጥበት፥ ስለዚህ ክፈችልኝ" እያለ።
\s5
\v 3 "ልብሴን አውልቄአለሁ፤ እንደገና መልበስ አለብኝ? እግሬን ታጥቤአለሁ፤ ማቆሸሽ አለብኝ?"
\v 4 ውዴ በበሩ መካፈቻ ቀዳዳ በኩል እጁን አስገባ፥ ልቤም ስለ እርሱ ታወከ።
\s5
\v 5 ለውዴ በሩን ልከፍትለት ተነሣሁ፥ እጆቼ ከርቤን አንጠባጠቡ፥ ጣቶቼ በበሩ እጀታ ላይ በከርቤ ረጠቡ።
\s5
\v 6 ለውዴ በሩን ከፈትኩለት፥ ውዴ ግን ተመልሶ ሄዶ ነበር። ልቤ ደነገጠ፤ እኔም ተከፋሁ። ፈለግሁት፥ ነገር ግን አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ ነገር ግን አልመለሰልኝም።
\s5
\v 7 ጠባቂዎቹ በከተማ ሲዘዋወሩ አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቆሰሉኝም፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ጠባቂዎችም ካባዬን ወሰዱብኝ። ወጣቷ ለከተማው ሴቶች ስትናገር፥
\s5
\v 8 እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች፥ ውዴን ካገኛችሁት ለእርሱ ካለኝ ፍቅር የተነሣ መታመሜን ልትነግሩት ቃል እንድትገቡልኝ እፈልጋለሁ። የከተማው ሴቶች ለወጣቷ ሲናገሩ፥
\s5
\v 9 አንቺ በሴቶች መካከል የተዋብሽዋ ሆይ፥ ውድሽ ከሌላው አፍቃሪ ወንድ የተሻለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን መሐላ እንድናደርግ የጠየቅሽን ውድሽ ከሌላው አፍቃሪ የተሻለው ለምንድነው? ወጣቷ ለከተማው ሴቶች ስትናገር፥
\s5
\v 10 ውዴ ደስተኛና ቀይ ነው፥ ከአሥር ሺዎችም የላቀ ነው።
\v 11 ራሱ ንጹህ ወርቅ ነው፤ ፀጉሩም ዞማና እንደ ቁራ የጠቆረ ነው።
\s5
\v 12 ዓይኖቹ በጅረት አጠገብ እንዳሉ እርግቦች፥ በወተት እንደ ታጠቡ፥ በማስቀመጫቸው ያሉ ዕንቁዎችን ይመስላሉ።
\s5
\v 13 ጉንጮቹ የሽቶ መዓዛ የሚሰጡ የልዩ ልዩ ቅመማ ቅመም መደብ ይመስላሉ። ከንፈሮቹ ከርቤን የሚያንጠባጥቡ አበቦች ናቸው።
\s5
\v 14 ክንዶቹ የዕንቁ ፈርጥ ባለበት ወርቅ ተሸፍኗል፤ ሆዱ በሰንፔር ያጌጠ የዝሆን ጥርስ ነው።
\s5
\v 15 እግሮቹ በንጹህ የወርቅ መሠረት ላይ የቆሙ፥ የእምነ በረድ ምሶሶዎች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስ፥ እንደ ተመረጠም ዝግባ ነው።
\s5
\v 16 አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፤ እርሱ ፍጹም ውብ ነው። የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ጓደኛዬም እርሱው ነው።
\s5
\c 6
\p
\v 1 በሴቶች መካከል እጅግ የተዋብሽዋ ሆይ፥ ውድሽ ወዴት ሄደ? ካንቺ ጋር እንድንፈልገው ውድሽ የሄደው በየትኛው አቅጣጫ ነው? ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 2 በአትክልቱ ሥፍራ መንጋውን ሊያሠማራ፥ አበቦችንም ሊሰበስብ፥ ውዴ ወደ አትክልቱ ሥፍራ፥ ወደ ቅመማ ቅመሞቹ መደቦች ወርዷል።
\v 3 እኔ የውዴ ነኝ፥ ውዴም የእኔ ነው፤ በአበቦቹ መካከል መንጋውን በደስታ ያሰማራል። የሴቲቱ አፍቃሪ እንዲህ ይላታል፥
\s5
\v 4 ውዴ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ቆንጆ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌም ውብ ነሽ፥ ሰንደቁን እንደያዘ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ።
\s5
\v 5 አድክመውኛልና ዓይኖችሽን ከእኔ መልሺ። ፀጉርሽ ከገለዓድ ተራራ ቁልቁል የሚወርደውን የፍየል መንጋ ይመስላል።
\s5
\v 6 ጥርሶችሽ ከመታጠቢያ ሥፍራቸው የሚመጡትን የሴት በግ መንጋ ይመስላሉ። እያንዳንዱ መንታ ወልዷል፥ በመካከላቸውም መካን የለም።
\v 7 በመሸፈኛሽ ውስጥ ጉንጮችሽ ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላሉ። የሴቲቱ አፍቃሪ ለራሱ ሲናገር፥
\s5
\v 8 ስልሳ ንግሥቶች፥ ሰማንያ ቁባቶች፥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ልጃገረዶች አሉ።
\v 9 እርግቤ፥ እንከን የሌለባት፥ ብቸኛዋ ናት፤ ለእናቷ ልዩ ልጅ፥ ለወለደቻት ሴትም የተመረጠች ነች። የሀገሬ ሴቶች ልጆች አይተው የተባረክሽ ነሽ አሏት፤ ንግሥቶችና ቁባቶችም ደግሞ አይተው አመሰገኗት፤ ንግሥቶቹና ቁባቶቹ እንዲህ አሏት፦
\s5
\v 10 የንጋት ብርሃን መስላ የምትወጣ፥ እንደ ጨረቃ ያማረች፥ እንደ ፀሐይ ያበራች፥ ሰንደቅ እንደ ያዘ ሠራዊት የምታስፈራ ይህቺ ማን ናት? የሴቲቱ አፍቃሪ ለራሱ ሲናገር፥
\s5
\v 11 በሸለቆው ውስጥ አዲስ የበቀለውን ለማየት፥ ወይኑ አፍርቶ እንደሆነ፥ ሮማኑም አብቦ እንደሆነ ለማየት፥ የለውዝ ተክል ወዳለበት ጥሻ ወረድሁ።
\v 12 በልዑሉ ሠረገላ እንደ ተቀመጥኩ ስለ ተሰማኝ፥ በጣም ደስ አለኝ። የሴቲቱ አፍቃሪ እንዲህ ይላል፥
\s5
\v 13 አንቺ ፍጹሟ ሴት፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ አተኩሬ እንዳይሽ ተመለሽ፥ እባክሽ ተመለሽ። ወጣቷ ሴት ፍቅረኛዋን እንዲህ ትለዋለች፥ በሁለት ረድፍ ጨፋሪዎች መካከል የምጨፍር ይመስል፥ ፍጹሟን ሴት ለምን ትክ ብለህ ታየኛለህ?
\s5
\c 7
\p
\v 1 አንቺ የልዑል ልጅ! እግሮችሽ በነጠላ ጫማ ውስጥ ሲታዩ እንዴት ያምራሉ? የዳሌዎችሽ ቅርጽ በእውቅ አንጥረኛ እጅ የተሠሩ ዕንቁዎችን ይመስላሉ።
\s5
\v 2 እንብርትሽ ክብ ጽዋ ይመስላል፤ ድብልቅ ወይን በፍጹም አይጉደለው። ሆድሽ በአበቦች የተከበበ የስንዴ ክምር ይመስላል።
\s5
\v 3 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ የሜዳ ፍየሎችን፥ ሁለት የአጋዘን ግልገሎችን ይመስላሉ።
\v 4 አንገትሽ በዝሆን ጥርስ የተሠራ የጥበቃ ማማ ይመስላል፤ ዓይኖችሽ በባትረቢ በር አጠገብ በሐሴቦን ያሉትን ኩሬዎች ይመስላሉ። አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ የሚመለከተውን በሊባኖስ ያለውን የመጠበቂያ ማማ ይመስላል።
\s5
\v 5 ራስሽ በአንቺ ላይ የቀርሜሎስን ተራራ ይመስላል፤ በራስሽ ላይ ያለው ጸጉር ጥቁር ሐምራዊ ነው። ንጉሡ በረጅሙ ጸጉርሽ ተይዞ ታስሮአል።
\v 6 ተወዳጇ ሆይ፥ እንዴት የምታስደስቺ፥ ውብና ያማርሽ ነሽ!
\s5
\v 7 ቁመትሽ የቴምር ዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም እንደ ተከማቹ ፍሬዎች ናቸው።
\v 8 እኔም፥ "በዚያ የዘንባባ ዛፍ ላይ እወጣለሁ፤ ቅርንጫፎቹንም እይዛለሁ" ብዬ አሰብኩ። ጡቶችሽ የወይን ክምችቶች ይሁኑ፥ የአፍንጫሽ እስትንፋስ መዓዛውም እንደ እንኮይ ይሁኑ።
\s5
\v 9 አፍሽ እንደ ምርጥ የወይን ጠጅ ይሁን፥ በዝግታም በውዴ ከንፈርና ጥርስ እየፈሰሱ ይንቆርቆሩ። ወጣቷ ፍቅረኛዋን እንዲህ ትለዋለች፥
\s5
\v 10 እኔ የውዴ ነኝ፥ እርሱም ይመኘኛል።
\v 11 ውዴ ሆይ ና፥ ወደ ገጠር እንሂድ፥ በመንደሮቹም እንደር።
\s5
\v 12 ወደ ወይኑ ቦታ ለመሄድ ማልደን እንነሣ፤ ወይናቸው አፍርቶ፥ አበባቸውም ፈክቶ፥ ሮማኑም አብቦ እንደሆነ እንይ። በዚያም ፍቅሬን እሰጥሃለሁ።
\s5
\v 13 ትርንጉዎች መዓዛቸውን ሰጡ፤ በምንቆይበት ቤት ደጃፍ ሁሉም ዓይነት የተመረጡ ፍሬዎች አሉ፥ አዲስና የቆዩ፥ ውዴ ሆይ፥ ለአንተ አስቀምጫቸዋለሁ።
\s5
\c 8
\p
\v 1 ምነው የእናቴን ጡቶች እንደጠባ እንደ ወንድሜ በሆንክ። ከዚያም በውጭ ባገኘሁህ ጊዜ ሁሉ በሳምኩህና፥ ማንም ባልናቀኝ ነበር።
\s5
\v 2 በመራሁህና ወደ እናቴ ቤት ባመጣሁህ፥ አንተም ባስተማርከኝ ነበር። የምትጠጣውን ጣፋጭ ወይን ጠጅ በሰጠሁህ፥ ከሮማኖቼም ጭማቂ ጥቂቱን።
\v 3 ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥ ግራ እጁ ይዞኛል፤ ቀኝ እጁም አቅፎኛል። ሴቲቱ ለሌሎች ሴቶች ስትናገር፥
\s5
\v 4 የኢየሩሳሌም ሴቶች ልጆች ሆይ፥ በፍቅር ግንኙነታችን ጊዜ እስክንረካ ድረስ ላታቋርጡን እንድትምሉልኝ እፈልጋለሁ። የኢየሩሳሌም ሴቶች ሲናገሩ፥
\s5
\v 5 በውዷ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትመጣ ይህቺ ማን ናት? ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥ ከእንኮዩ ዛፍ ጥላ ሥር አነቃሁህ፤ በዚያ እናትህ ፀነሰችህ፤ በዚያም አንተን ወለደችህ፤ ተገላገለችህ።
\s5
\v 6 በልብህ ላይ እንደ ማኅተም አስቀምጠኝ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ ላይ፥ ፍቅር እንደ ሞት ብርቱ ነውና። የታማኝነቷም ጠንካራ ስሜት እንደ ሲዖል ጨካኝ ነው፤ ነበልባሏ ይነዳል፤ የምትንቦገቦግ ነበልባል ናት፥ ነበልባሏ ከሌላ ከየትኛውም እሳት ይልቅ የጋለ ነው።
\s5
\v 7 የማዕበል ውሃ ፍቅርን ለማጥፋት አይችልም፥ ጎርፍም ሊያሰጥመው አይችልም። ሰው በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ብሎ ቢሰጥ ስጦታው ፈጽሞ ይናቃል። የወጣቷ ወንድሞች እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፥
\s5
\v 8 ታናሽ እህት አለችን፥ ጡቶቿም ገና አላደጉም። ለጋብቻ በምትሰጥበት በዚያን ቀን ለእህታችን ምን ልናደርግላት እንችላለን?
\s5
\v 9 እርሷ ቅጥር ብትሆን፥ በላይዋ ላይ የጥበቃ ማማ እንሠራባታለን። በር ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እናስውባታለን። ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 10 እኔ ቅጥር ነኝ፥ አሁን ግን ጡቶቼ እንደ ተመሸጉ ግንቦች ናቸው፤ ስለዚህ በዓይኖቹ ፊት በሚገባ አድጌአለሁ። ወጣቷ ለራሷ ስትናገር፥
\s5
\v 11 ሰለሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ እርሱም የወይኑን ቦታ ለሚንከባከቡት አከራየው። እያንዳንዱ ስለ ፍሬው አንድ አንድ ሺህ ሰቅል ብር ያመጣለት ነበር።
\v 12 የእኔ የወይን ቦታ የእኔው የግሌ ነው፤ ወዳጄ ሰለሞን ሆይ፥ አንድ ሺህ ሰቅሉ ያንተ ይሆናል፥ ሁለት መቶ ሰቅሉ ፍሬውን ለሚንከባከቡት ነው። የሴቲቱ አፍቃሪ ሲናገራት፥
\s5
\v 13 በአትክልቱ ቦታ የምትኖሪ ሆይ፥ ጓደኞቼ ድምጽሽን እየሰሙት ነው፤ እኔም ከሚሰሙት አንዱ ልሁን። ሴቲቱ ለፍቅረኛዋ ስትናገር፥
\s5
\v 14 ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመማ ቅመም ተራራዎች ላይ የአጋዘንን ወይም የሜዳ ፍየል ግልገልን ምሰል።