am_ulb/17-EST.usfm

345 lines
45 KiB
Plaintext

\id EST
\ide UTF-8
\h አስቴር
\toc1 አስቴር
\toc2 አስቴር
\toc3 est
\mt አስቴር
\s5
\c 1
\p
\v 1 በአርጤክስስ ዘመን (እርሱም ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች የነገሠው ነው)
\v 2 በእነዚያ ጊዜያት ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ ውስጥ ባለው የመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።
\s5
\v 3 በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አደረገላቸው። የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፥ ባላባቶችና የአውራጃ አስተዳዳሪዎችም በፊቱ ነበሩ።
\v 4 የመንግሥቱን ውበት ባለጸግነትና የግርማውን ክብር ታላቅነት ለብዙ ቀናት ማለትም ለ180 ቀናት አስጎበኛቸው።
\s5
\v 5 እነዚህ ቀናት ካበቁ በኋላ ንጉሡ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ግብዣ አዘጋጀ። ግብዣው የተዘጋጀው ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በሱሳ ቤተመንግሥት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ነበር። ይህም የተደረገው በንጉሡ ቤተመንግሥት መናፈሻ በሚገኘው አደባባይ ውስጥ ነበር።
\v 6 ከጥጥ የተሠሩ ነጭና ሰማያዊ መጋረጃዎች ነጭና ሐምራዊ ገመድ በብር ቀለበቶቹ ውስጥ አልፈው በእምነበረዱ ቋሚዎች ላይ በመሰቀላቸው የመናፈሻው አደባባይ ተውቦ ነበር። በቀይ ዓለት፥ በእምነበረድ፥ በእንቁ እናትና የተለያየ ቀለም ባላቸው የንጣፍ ድንጋዮች ባሉት ሥዕላዊ ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ አልጋዎች ነበሩ።
\s5
\v 7 መጠጡ በወርቃማ መጠጫዎች ይቀርብ ነበር። እያንዳንዱ መጠጫ የተለያየ ነበር፥ ከንጉሡ ለጋስነት የተነሣም የቤተመንግሥቱ ወይን የተትረፈረፈ ነበር።
\v 8 መጠጡ ይቀርብ የነበረውም፥ "ግዴታ መኖር የለበትም" የሚለውን መመሪያ በመከተል ነበር። እንግዶቹ እያንዳንዳቸው በሚፈልጉት መጠን እንዲቀርብላቸው ንጉሡ የቤተመንግሥቱን ሠራተኞች አዝዞ ነበር።
\s5
\v 9 ንግሥት አስጢን በበኩሏ በንጉሡ አርጤክስስ ንጉሣዊ ቤተመንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች።
\v 10 በሰባተኛው ቀን ንጉሡ ከወይን ጠጅ የተነሣ ልቡን ደስታ በተሰማው ጊዜ ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርንና ከርከስን (በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ሹማምንት) ንግሥት አስጢን ዘውዷን ደፍታ በፊቱ እንድትቀርብ አዘዛቸው።
\v 11 ተክለ ሰውነቷ ያማረ ነበርና ውበቷን ለሕዝቡና ለሹማምንቱ ለማሳየት ፈለገ።
\s5
\v 12 ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በሹማምንቱ በላከባት ቃል መሠረት ለመምጣት እምቢ አለች። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቆጣ፥ ቁጣውም በውስጡ ነደደ።
\s5
\v 13 ስለዚህ ንጉሡ ዘመኑን ከሚመረምሩ ጥበበኞች ሰዎች ጋር ተመካከረ (ሕግንና ዳኝነትን ስለሚያውቁት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ልምድ እንዲህ ነበርና) ።
\v 14 የቅርቦቹ የነበሩትም ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት የሆኑት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓርና ምሙካን ነበሩ። እነዚህ ለንጉሡ የሚቀርቡና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙ ናቸው።
\v 15 "በሹማምንቱ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትዕዛዝ አልታዘዘችምና በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ መደረግ ያለበት ምንድነው?"
\s5
\v 16 ምሙካንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፥ "ንግሥቲቱ አስጢን የበደለችው መኳንንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ ግዛቶች ሁሉ የሚገኘውን ሕዝብ በሙሉ ደግሞ እንጂ ንጉሡን ብቻ አይደለም።
\v 17 የንግሥቲቱ ጉዳይ በሁሉም ሴቶች የሚታወቅ ይሆናል። ይህም ባሎቻቸውን እንዲንቁ ያደርጋል። እነርሱም፥ 'ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት ንጉሡ አርጤክስስ አዘዘ፥ እርስዋ ግን እምቢ አለች' ይላሉና።
\v 18 የንግሥቲቱን ጉዳይ የሰሙ የመኳንንቱ ሚስቶችም ይህ ቀን ከማለፉ በፊት ለንጉሡ መካንንቶች በሙሉ ተመሳሳዩን ቃል ይናገራሉ። ብዙ ንቀትና ቁጣም ይሆናል።
\s5
\v 19 ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ፥ አስጢን ዳግመኛ በፊቱ እንዳትቀርብ ንጉሣዊ ትዕዛዝ ያውጣ፥ ሊለወጥ የማይቻል ሆኖም በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ ይጻፍ። የንግሥትነቷን ክብርም ንጉሡ ክእርስዋ ለምትሻል ለሌላይቱ ይስጥ።
\v 20 የንጉሡ ትዕዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በሚታወጅበት ጊዜ፥ ከታላቁ እስከ ታናሹ ድረስ ሚስቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።"
\s5
\v 21 ንጉሡና መካንንቶቹ በዚህ ምክር ተደሰቱ፥ ንጉሡም የምሙካንን ምክር ተግባራዊ አደረገው።
\v 22 እርሱም ደብዳቤዎችን ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሕፈትና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ አድርጎ ወደ መንግሥቱ አውራጃዎች በሙሉ ላከው። እርሱም እያንዳንዱ በቤተሰቡ ላይ ገዥ እንዲሆን አዘዘ። ይህም ትዕዛዝ በመንግሥቱ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየቋንቋው ተሰጠው።
\s5
\c 2
\p
\v 1 ከእነዚህ ነገሮች በኋላ የንጉሡ አርጤክስስ ቁጣ በበረደለት ጊዜ ንግሥት አስጢንን፥ እርሷም ያደረገችውን አሰበ። እንዲሁም በእርሷ ላይ ያስተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ አሰበ።
\v 2 ከዚያም ያገለግሉት የነበሩት የንጉሡ ወጣቶች፥ "የተዋቡ ልጃገረዶች ለንጉሡ ይፈለጉለት።
\s5
\v 3 የተዋቡ ልጃገረዶችን በሙሉ በሱሳ ቤተመንግሥት ወደሚገኘው የሴቶች መኖሪያ እንዲሰበስቧቸው በመንግሥቱ አውራጃዎች ሁሉ ንጉሡ ኃላፊዎችን ይሹም። እነርሱም የሴቶች ኃላፊ በሆነው የንጉሡ ሹም በሄጌ ጥበቃ ሥር ይደረጉ፥ እርሱም መዋቢያዎቻቸውን ይስጣቸው።
\v 4 ንጉሡን ደስ የምታሰኘው ልጃገረድ በአስጢን ፈንታ ንግሥት ትሁን።" ይህም ምክር ንጉሡን አስደሰተው፥ እርሱም እንደዚሁ አደረገ።
\s5
\v 5 በሱሳ ከተማ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ነበር፥ እርሱም ብንያማዊ ሲሆን የቂስ ልጅ፥ የሰሜኢ ልጅ፥ የኢያዕር ልጅ ነበር።
\v 6 እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረከው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ተማርከው ከተወሰዱት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም ተወስዶ ነበር።
\s5
\v 7 እርሱም አባትም ሆነ እናት አልነበራትምና የአጎቱን ልጅ ሀደሳ የተባለችውን አስቴርን ያሳድግ ነበር። ልጃገረዲቱም የተዋበ ተክለሰውነትና ማራኪ ገጽታ ነበራት። መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወስዷት ነበር።
\s5
\v 8 የንጉሡ መመሪያና ትዕዛዝ በታወጀ ጊዜ ብዙ ልጃገረዶችን ወደ ሱሳ ቤተመንግሥት ሰበሰቧቸው። እነርሱም ከሄጌ ጥበቃ ሥር ተደረጉ። አስቴርም ደግሞ ወደ ቤተመንግሥቱ ተወስዳ ከሴቶቹ ተቆጣጣሪ ከሄጌ ሥር ተደረገች።
\v 9 ልጃገረዲቱ ደስ አሰኘችው፥ በፊቱም ሞገስን አገኘች። ወዲያውም የምግብ ድርሻዋንና መዋቢያዎቿን ሰጣት። ለእርሷም ከንጉሡ ቤተመንግሥት የሚያገለግሏትን ሰባት ልጃገረዶች መደበላት፥ እርሷንና የሚያገለግሏትን ልጃገረዶች በሴቶቹ መኖሪያ ውስጥ ወደ ተሻለው ክፍል አዛወራቸው።
\s5
\v 10 መርዶክዮስ እንዳትናገር አዝዟት ስለ ነበር፥ አስቴር ሕዝቧንም ሆነ ወገንዋን ለማንም አልተናገረችም ነበር።
\v 11 መርዶክዮስ የአስቴርን ደኅንነትና ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ በየዕለቱ በሴቶቹ መኖሪያ በስተውጭ ባለው አደባባይ ይመላለስ ነበር።
\s5
\v 12 እያንዳንዷ ልጃገረድ ወደ ንጉሡ አርጤክስስ የምትሄድበት ተራ በደረሰ ጊዜ - ለሴቶቹ በወጣው ደንብ መሠረት እያንዳንዷ ልጃገረድ ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወር ደግሞ በሽቶዎችና በመዋቢያዎች ለአሥራ ሁለት ወራት የውበት አያያዝ ጊዜአቸውን ማጠናቀቅ ነበረባቸው -
\v 13 አንዲት ልጃገረድ ወደ ንጉሡ በምትሄድበት ጊዜ ወደ ቤተመንግሥት እንድትወስደው የፈለገችው ሁሉ ከሴቶቹ መኖሪያ ይሰጣት ነበር።
\s5
\v 14 ሲመሽ ትገባና ሲነጋ ወደ ሁለተኛው የሴቶች መኖሪያ፥ በቁባቶቹ ላይ ኃላፊ ወደሆነው የንጉሥ ሹም ወደ ሻአሽጋዝ ጥበቃ ሥር ትመለስ ነበር። ንጉሡ ተደስቶባት ዳግም ካልጠራት በስተቀር ሁለተኛ ወደ እርሱ መመለስ አትችልም ነበር።
\s5
\v 15 ወደ ንጉሡ ለመግባት የአስቴር (መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ የወሰዳት የአቢካኤል ልጅ) ተራ በደረሰ ጊዜ በሴቶች ላይ ኃላፊ የሆነው የንጉሡ ሹም ሄጌ ከነገራት በቀር ምንም ነገር አልጠየቀችም። አስቴርም በሚያዩዋት ሁሉ ፊት ሞገስን ታገኝ ነበር።
\v 16 አስቴርም ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ ቴቤት ተብሎ በሚጠራው በአሥረኛው ወር፥ ወደ ንጉሣዊ መኖሪያው ተወሰደች።
\s5
\v 17 ንጉሡም ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደዳት፥ ከደናግሉም ሁሉ ይልቅ በፊቱ ሞገስንና መወደድን አገኘች፥ ስለዚህ የእቴጌነትን ዘውድ በራሷ ላይ አደረገላት፥ በአስጢንም ምትክ ንግሥት አደረጋት።
\v 18 ንጉሡም "የአስቴር ግብዣ" ብሎ የጠራውን ታላቅ ግብዣ ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ ሁሉ አደረገ፥ አውራጃዎቹንም ከቀረጥ አሳረፋቸው። ደግሞም በንጉሣዊ ልግስናው ስጦታዎችን ሰጠ።
\s5
\v 19 ደናግሎቹ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ይቀመጥ ነበር።
\v 20 አስቴር ሕዝቧን ወይም ወገኗን መርዶክዮስ ባዘዛት መሠረት ገና ለማንም አልተናገረችም ነበር። እርሷም በልጅነትዋ ጊዜ ታደርግ አንደነበረው የመርዶክዮስን ምክር መከተልዋን ቀጠለች።
\v 21 በእነዚያም ቀናት መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ እያለ በሩን ይጠብቁ የነበሩት ሁለቱ የንጉሡ ሹማምንት ገበታና ታራ ተቆጡ፥ ንጉሡን አርጤክስስንም ለመግደል ፈለጉ።
\s5
\v 22 መርዶክዮስ ጉዳዩን ባወቀ ጊዜ ለንግሥት አስቴር ነገራት፥ እርሷም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረችው።
\v 23 መረጃው ሲመረመር እውነት ሆኖ ተገኝ፥ ሁለቱም ሰዎች በስቅላት ተቀጡ። ታሪኩም በንጉሡ ፊት በታሪክ መዝገብ ላይ ተጻፈ።
\s5
\c 3
\p
\v 1 ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ንጉሡ አርጤክስስ አጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን በሹመት አላቀው፥ የሥልጣኑንም ወንበር ከእርሱ ጋር ከነበሩት ሹማምንት ሁሉ በላይ አደረገለት።
\v 2 በንጉሡ በር የሚጠብቁ የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉ ንጉሡ በሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ሁልጊዜ ለሐማ በመንበርከክ አክብሮታቸውን ያሳዩት ነበር። መንዶክዮስ ግን አልተንበረከከለትም፥ አክብሮትም አላሳየውም።
\s5
\v 3 ከዚያም በንጉሡ በር የሚጠብቁት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፥ "የንጉሡን ትዕዛዝ የማታከብረው ለምንድነው?" አሉት።
\v 4 ይህንን በየቀኑ ቢናገሩትም እርሱ ግን ቃላቸውን ለመቀበል እምቢ አለ። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ስለነበረ መርዶክዮስ በዚህ ሁኔታ እንዴት እንደሚቀጥል ለማየት ጉዳዩን ለሐማ ነገሩት።
\s5
\v 5 ሐማም መርዶክዮስ ተንበርክኮ እንዳልሰገደለት ባየ ጊዜ ሐማ በንዴት ተሞላ።
\v 6 የመርዶክዮስን የዘር ማንነት የንጉሡ አገልጋዮች ነግረውት ስለ ነበረ መርዶክዮስን ብቻ የመግደልን ሃሳብ ናቀው። በመላው አርጤክስስ መንግሥት ውስጥ የነበሩትን የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ በሙሉ ለመደምሰስ ፈለገ።
\s5
\v 7 ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር (እርሱም የኒሳን ወር ነው) ፥ ፉር የሚባለውን፥ ቀኑንና ወሩን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የእያንዳንዱን ቀንና ወር ዕጣ በሐማ ፊት ጣሉ። በዕጣው መሠረት የአዳርን (አሥራ ሁለተኛውን ወር) መረጡ።
\s5
\v 8 ከዚያም ሐማ ንጉሡን አርጤክስስን፥ "በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተበታትኖና ተሠራጭቶ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ። ሕጋቸው ከሌላው ሕዝብ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕጎች አያከብሩም፥ ስለዚህ ንጉሡ በሕይወት እንዲኖሩ ሊተዋቸው አይገባውም።
\v 9 ንጉሡ ደስ የሚለው ከሆነ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ይስጥ፥ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ገቢ እንዲያደርጉት በንጉሡ ንብረት ኃላፊዎች በሆኑት እጅ አሥር ሺህ መክሊት ብር መዝኜ እሰጣለሁ"አለው።
\s5
\v 10 ከዚያም ንጉሡ ማኅተም ያለበትን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ ለአይሁዶቹ ጠላት፥ ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው።
\v 11 ንጉሡም ሐማን፥ "ገንዘቡ ለአንተና ለሕዝብህ ተመልሶ ማየት እፈልጋለሁ። አንተም በእርሱ የፈለግኸውን ሁሉ ታደርግበታለህ" አለው።
\s5
\v 12 ከዚያም በመጀመሪያው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፥ ለንጉሡ የአውራጃ አስተዳዳሪዎች፥ በአውራጃዎቹ ሁሉ ላይ ለነበሩት፥ ልዩ ልዩ ሕዝቦችን ለሚያስተዳድሩትና ለሕዝቡ ሁሉ ሹማምንት፥ ለየአውራጃዎቹ በየራሳቸው ጽሑፍና ለእያንዳንዱም ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ ሐማ ያዘዘው ሁሉ በዐዋጁ ውስጥ ተጻፈ። ዐዋጁም በንጉሡ አርጤክስስ ስም ተጽፎ በቀለበቱ ታተም።
\v 13 በአሥራ ሁለተኛው ወር (እርሱም የአዳር ወር ነው) ፥ በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ በአንድ ቀን ውስጥ አይሁዶችን በሙሉ፥ ከወጣት እስከ ሽማግሌ፥ ልጆችንና ሴቶችን በአንድ ቀን እንዲያጠፉ፥ እንዲገድሉና እንዲደመስሱና ንብረታቸውንም እንዲዘርፉ ደብዳቤዎቹም በመልዕክተኞቹ እጅ ለንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ ተላከ።
\s5
\v 14 የደብዳቤው ቅጅም በየአውራጃው ሕግ ተደረገ። ለዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ በየአውራጃው ያሉ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁት ተደረገ።
\v 15 መልዕክተኞቹም የንጉሡን ዐዋጅ ለማሰራጨት በጥድፊያ ሄዱ። አዋጁ በሱሳ ቤተመንግሥት ውስጥም ደግሞ ተሰራጨ። ንጉሡና ሐማ ለመጠጣት ተቀመጡ፥ የሱሳ ከተማ ግን ተበጥብጣ ነበር።
\s5
\c 4
\p
\v 1 መርዶክዮስ የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ልብሶቹን ቀደደ፥ ማቅ ለብሶም በራሱ ላይ አመድ ነሰነሰ። ወደ ከተማይቱ መካከል በመሄድም በታላቅ ጩኸት መራራ ልቅሶ አለቀሰ።
\v 2 ማቅ ለብሶ በንጉሡ በር በኩል ማለፍ አይፈቀድም ነበርና እስከ አቅራቢያው ድረስ ብቻ ሄደ።
\v 3 የንጉሡ ዐዋጅና ትዕዛዝ በደረሰበት አውራጃ ሁሉ በአይሁድ መካከል ከጾም፥ ከልቅሶና ከዋይታ ጋር ታላቅ ሀዘን ሆነ። ብዙዎቹም በማቅና በአመድ ላይ ተኙ።
\s5
\v 4 የአስቴር ወጣት ሴቶችና አገልጋዮቿ መጥተው ስለ ሁኔታው በነገሯት ጊዜ ንግሥቲቱ እጅግ አዘነች። እርሷም መርዶክዮስን እንዲያለብሱት (ማቁን አውጥቶ እንዲጥል ነበር) ልብሶችን ላከችለት፥ እርሱ ግን አልተቀበለም።
\v 5 ከዚያም አስቴር እርሷን ለማገልገል የተመደበውንና ከንጉሡ ሹማምንት አንዱ የሆነውን ሀታክን ጠራችው። ምን እንደ ተፈጠረና ምን ማለትም እንደሆነ ያጣራ ዘንድ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ አዘዘችው።
\s5
\v 6 ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው የከተማው አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ሄደ።
\v 7 መርዶክዮስም የገጠመውን ነገር ሁሉ፥ አይሁድን ለመግደል ሐማ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ቃል የገባውን የገንዘብ መጠን አስታወቀው።
\v 8 በተጨማሪም አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የታወጀውን የዐዋጁን ቅጅም ሰጠው። ይህንንም ያደረገው ሀታክ ለአስቴር እንዲያሳያትና ወደ ንጉሡ ሄዳ ስለ ሕዝቧ ምህረት እንዲያደርግ እንድትለምነውና እንድትማልደው ኃላፊነት እንዲሰጣት ነበር።
\s5
\v 9 ሀታክ ሄደና መርዶክዮስ ነግሮት የነበረውን ለአስቴር ነገራት።
\v 10 ከዚያም አስቴር ሀታክ ተመልሶ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ ነገረችው።
\v 11 እንዲህም አለችው፥ "ወንድ ሆነ ሴት ማንኛውም ሰው ሳይጠራ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ቢገባ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለ የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉና በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ያውቃሉ፥ ሕጉም በሕይወት እንዲኖር ንጉሡ የወርቅ በትሩን ከሚዘረጋለት በስተቀር መገደል አለበት የሚል ነው። እነዚህን ሠላሳ ቀናት ወደ ንጉሡ ለመቅረብ አልተጠራሁም።"
\v 12 ስለዚህ ሀታክ የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ አስታወቀው።
\s5
\v 13 መርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልዕክት መለሶ ለከባት፥ "በንጉሡ ቤተመንግሥት ውስጥ ስለሆንሽ ከሌሎቹ አይሁዶች ሁሉ ይልቅ እንደምትድኚ ማሰብ የለብሽም።
\v 14 አንቺ በዚህ ጊዜ ዝምታን ብትመርጪ ለአይሁድ እርዳታና መዳን ከሌላ ሥፍራ ይነሣላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ። ወደ ንግሥትነት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ቀን እንደሆነስ ማን ያውቃል?"
\s5
\v 15 ከዚያም አስቴር ይህን መልዕክት ወደ መርዶክዮስ ላከች፥
\v 16 "ሂድ፥ በሱሳ የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ በአንድ ላይ ሰብስባቸውና ስለ እኔ ጹሙ። ለሦስት ቀንና ሌሊት አትብሉ፥ አትጠጡም። እኔና ወጣት ልጃገረዶቼም እንደዚሁ እናደርጋለን። ከዚያም ከሕጉ ውጪ ቢሆንም ወደ ንጉሡ እገባለሁ፥ ከጠፋሁም እጠፋለሁ።"
\v 17 መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር ያለችውን ሁሉ አደረገ።
\s5
\c 5
\p
\v 1 ከሥስት ቀን በኋላ አስቴር የንግሥትነትዋን ልብስ ለብሳ በንጉሡ መኖሪያ ፊት ለፊት፥ በንጉሡ ቤተመንግሥት ውስጠኛው አደባባይ ልትቆም ሄደች። ንጉሡም በቤቱ መግቢያ በር ትይዩ በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።
\v 2 ንጉሡ ንግሥት አስቴርን አደባባዩ ላይ ቆማ ባያት ጊዜ፥ በፊቱ ሞገስን አገኘች። እርሱም የወርቁን በትር አንስቶ ዘረጋላት። ስለዚህ አስቴር ቀረበችና የበትሩን ጫፍ ነካች።
\s5
\v 3 ከዚያም ንጉሡ፥ "ንግሥት አስቴር! ምንድነው የምትፈልጊው? ጥያቄሽስ ምንድነው? የመንግሥቴን ግማሽ ከሆነም ይሰጥሻል።"
\v 4 አስቴርም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ ንጉሡ ከሐማ ጋር ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ዛሬ ይምጣ" አለችው።
\s5
\v 5 ከዚያም ንጉሡ፥ "አስቴር ያለችው እንዲደረግ፥ በአስቸኳይ ሐማን ጥሩት" አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሄዱ።
\v 6 በግብዣው ላይ ወይኑ እየቀረበ እያለ ንጉሡ አስቴርን፥ "ልመናሽ ምንድነው? ይሰጥሻል። ጥያቄሽ ምንድነው? እስከ መንግሥቴ ግማሽ ይሰጥሻል" አላት።
\s5
\v 7 አስቴርም፥ "በንጉሡ ዓይን ሞገስን ካገኘሁ፥
\v 8 የለመንኩትን ሊሰጠኝና ጥያቄዬን ሊያከብርልኝ ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆን ልምናዬና ጥያቄዬ ይህ ነው። ነገ በማዘጋጅልህ ግብዣ ላይ ንጉሡ ከሐማ ጋር ይምጣ፥ እኔም የንጉሡን ጥያቄ እመልሳለሁ" አለችው።
\s5
\v 9 ሐማ በዚያን ቀን ደስ ብሎት፥ ልቡም ሐሴት አድርጎ ሄደ። ነገር ግን ሐማ መርዶስዮስን በፊቱ ሳይፈራና ሳይንቀጠቀጥ፥ ከተቀመጠበትም ሳይነሳ በንጉሡ በር ባየው ጊዜ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተናደደ።
\v 10 ሆኖም ሐማ ራሱን ተቆጣጠረና ወደ ራሱ ቤት ሄደ።
\v 11 ጓደኞቹን አስጠራና ከሚስቱ ዞሳራ ጋር በአንድ ላይ ሰበሰባቸው። ሐማም የብልጽግናውን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ከንጉሡ አገልጋዮችና ከሹማምንቱ ሁሉ በላይ እንዴት በማዕረግ አንደበለጣቸው አወራላቸው።
\s5
\v 12 ሐማም፥ "ንግሥት አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ እንኳን ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር እንዲመጣ የጋበዘችው የለም። ነገም ደግሞ ከንጉሡ ጋር ግብዣዋ ላይ እንድገኝ ጋብዛኛለች።
\v 13 ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ ልምምዴ ምንም አይጠቅመኝም።"
\s5
\v 14 ከዚያም ሚስቱ ዞሳራ ሐማንና ጓደኞቹን ሁሉ፥ "ቁመቱ ሃምሳ ክንድ የሆነ መስቀያ ያዘጋጁ። መርዶክዮስን በዚያ ላይ እንዲሰቅሉት ነገ ጠዋት ለንጉሡ ንገረው። ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ሂድ" አለቻቸው። ይህም ሐማን አስደሰተው፥ መስቀያው እንዲዘጋጅም አስደረገ።
\s5
\c 6
\p
\v 1 በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፉን መተኛት አልቻለም። እርሱም በዘመነ መንግሥቱ የተከናወኑ ሁነቶች በታሪክነት የተመዘገቡበትን መዝገብ እንዲያመጡለት አገልጋዮቹን አዘዛቸው፥ እነርሱም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለንጉሡ ያነቡለት ነበር።
\v 2 ገበታና ታራ፥ ሁለቱ በር ጠባቂ የንጉሥ ሹሞች ንጉሥ አርጤክስስን ለመግደል ማቀዳቸውን መርዶክዮስ መናገሩ ተመዝግቦ ተገኘ።
\v 3 ንጉሡም፥ "ይህንን ስላደረገ ለመርዶክዮስ ክብርና እውቅና ለመስጠት ምን ተደረገለት?" ብሎ ጠየቀ። ከዚያም ንጉሡን የሚያገለግሉ ወጣቶች፥ "ምንም አልተደረገለትም" አሉት።
\s5
\v 4 ንጉሡም፥ "በአደባባዩ ውስጥ ያለው ማነው?" አለ። በዚያን ጊዜ ሐማ መርዶክዮስን ባዘጋጀለት መስቀል ላይ ለማሰቀል ለንጉሡ ለመንገር ወደ ውጪኛው አደባባይ ገብቶ ነበር።
\v 5 የንጉሡም አገልጋዮች፥ "ሐማ አደባባዩ ውስጥ ቆሟል" አሉት። ንጉሡም፥ "ይግባ" አለ።
\v 6 ሐማ በገባ ጊዜም ንጉሡ፥ "ንጉሥ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው ምን ይደረግለት?"አለው። ሐማም በልቡ፥"ከእኔ የበለጠ ንጉሡ ሊያከብረው የሚወደው ማን ይኖራል?" ብሎ አሰበ።
\s5
\v 7 ሐማም ንጉሡን፥ "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው፥
\v 8 ንጉሡ ይለብሰው የነበረ ንጉሣዊ ልብስ ይምጣለት፥ ንጉሡ ይቀመጥበት የነበረና በራሱ ላይ የክብር ጌጥ የተደረገለት ፈረስ ይምጣለት።
\v 9 ከዚያም ልብሶቹና ፈረሱ ከንጉሡ ሹማምንት እጅግ በተመረጡት በአንደኛው እጅ ይሰጡ፥ እነርሱም ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፥ በፈረሱ ላይ በማስቀመጥም በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች ይምሩት፥ በፊቱም "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው የሚደረግለት እንዲህ ነው!" እያሉ ያውጁ" አለ።
\s5
\v 10 ከዚያም ንጉሡ ሐማን፥ "ፍጠን፥ እንደተናገርከው ልብሶቹንና ፈረሱን ውሰድ፥ በንጉሡ በር ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ ይህንኑ አድርግለት። ከተናገርከውም አንድ አንዳይጎድል" አለው።
\v 11 ከዚያም ሐማ ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ። መርዶክዮስን አልብሶና ፈረስ ላይ አስቀምጦ በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች አዟዟረው። በፊቱም፥ "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው የሚደረግለት እንዲህ ነው!" እያለ ዐወጀ።
\s5
\v 12 መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን ፊቱን ሸፍኖና አዝኖ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ።
\v 13 ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለጓደኞቹ ሁሉ የገጠመውን ነገር በሙሉ ነገራቸው። በጥበባቸው የታወቁት ሰዎቹና ምስቱ ዞሳራም፥ "በፊቱ መውደቅ የጀመርከለት መርዶክዮስ አይሁዳዊ ከሆነ በርግጥ በፊቱ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም" አሉት።
\v 14 ከእርሱ ጋር እየተነጋገሩ እያሉ የንጉሡ ሹማምንት መጡ። እነርሱም አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሐማን አቻኮሉት።
\s5
\c 7
\p
\v 1 ስለዚህ ንጉሡና ሐማ በንግሥት አስቴር ለመጋበዝ ሄዱ።
\v 2 በዚህ በሁለተኛው ቀን፥ ወይን እየጠጡ እያሉ፥ ንጉሡ አስቴርን፥ "ልመናሽ ምንድነው ንግሥት አስቴር? እርሱ ይሰጥሻል። ጥያቄሽስ ምንድነው? እስከ መንግሥት አጋማሽ ድረስ ይሰጥሻል?" አላት።
\s5
\v 3 ንግሥት አስቴርም መልሳ፥ "ንጉሥ ሆይ፥ በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ ከሆነና ደስ የምትሰኝበትም ከሆነ ሕይወቴ እንድትሰጠኝ ልመናዬ ይህ ነው፥ ስለ ሕዝቤም የምጠይቀው ይህንኑ ነው።
\v 4 እኔና ሕዝቤ ለመጥፋት፥ ለመሞትና ለመደምሰስ ተሽጠናልና። ወንድና ሴት ባሪያዎች እንድንሆን ለባርነት ብቻ ተሽጠን ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩኝ ነበር፥ ይህንን በመሰለው ጭንቀት ንጉሡን ማወክ አይገባምና።
\v 5 ከዚያም ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርን፥ "ማነው እርሱ? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ ልቡ የሞላ ያ ሰው የት ነው የሚገኘው?" አላት።
\s5
\v 6 አስቴርም፥ "ያ ጠላትና ባላጋራው ሰው ይህ ክፉው ሐማ ነው!" ሐማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት ደነገጠ።
\v 7 ንጉሡም በቁጣ ወይን ከሚጠጣበት ግብዣ ተነሥቶ ወደ ቤተመንግሥቱ መናፈሻ ሄደ፥ ሐማ ግን ንግሥት አስቴር ሕይወቱን እንድትታደገው ሊለምናት በዚያው ቆይቶ ነበር። ከንጉሡ ጥፋት እንደተወሰነበት አይቷልና።
\s5
\v 8 ከዚያም ንጉሡ ከቤተመንግሥቱ መናፈሻ ወደ ወይን መጠጫው ክፍል ተመለሰ። ሐማ አስቴር በነበረችበት ድንክ አልጋ ላይ ልክ መደፋቱ ነበር። ንጉሡም፥ "በገዛ ቤቴ፥ በእኔው ፊት ንግሥቲቱን ሊደፍራት ነው እንዴ?" አለ። ልክ ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ እንደወጣ፥ አገልጋዮቹ የሐማን ፊት ሸፈኑት።
\s5
\v 9 ከዚያም ንጉሡን ከሚያገለግሉት ሹማምንቶች አንዱ የሆነው ሐርቦና፥ "ሃምሳ ክንድ ቁመት ያለው መስቀያ በሐማ ቤት ቆሟል። ያቆመውም ንጉሡን ለመታደግ የተናገረውን መርዶክዮስን ለመስቀል ነው" አለ። ንጉሡም "በእርሱ ላይ ስቀሉት" አላቸው።
\v 10 ስለዚህ ሐማን ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው መስቀያ ላይ ሰቀሉት። ከዚያም የንጉሡ ቁጣ በረደ።
\s5
\c 8
\p
\v 1 በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁዶችን ጠላት፥ የሐማን ንብረት፥ ለንግሥት አስቴር ሰጣት። መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበረ፥ መርዶክዮስ በንጉሡ ፊት ማገልገል ጀመረ።
\v 2 ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ማኅተም ያለበትን ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው። አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ይዞታ ላይ ኃላፊ አድርጋ ሾመችው።
\s5
\v 3 ከዚያም አስቴር ንጉሡን ደግማ ተናገረችው። እርሷም በምድር ላይ ተደፍታ አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ ያሴረውን የጥፋት ዕቅድ ማብቂያ እንዲያደርግለት እያለቀሰች ለመነችው።
\v 4 ከዚያም ንጉሡ የወርቁን በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት። እርሷም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመች።
\s5
\v 5 እርሷም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነና በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ፥ ነገሩም በንጉሡ ፊት ትክክል መስሎ ከታየውና እኔም በዓይንህ ፊት ተወድጄ ከሆነ፥ በአጋጋዊው በሐመዳቱ ልጅ በሐማ የተጻፈውን፥ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚኖሩትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈውን ድብዳቤ የሚሽር አዋጅ ይጻፍ።
\v 6 በሕዝቤ ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማየት እንዴት መታገሥ እችላለሁ? የዘመዶቼን ጥፋት መመልከቱንስ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?" አለችው።
\s5
\v 7 ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን፥ "ተመልከቱ፥ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጠኋት፥ አይሁድን ሊያጠቃ ስለነበርም እርሱን በመስቀያው ላይ ሰቀሉት።
\v 8 ለአይሁዶች በንጉሡ ስም ሌላ ዐዋጅ ጻፉ፥ በንጉሡም የቀለበት ማኅተም አትሙበት። ቀደም ሲል በንጉሡ ስም የተጻፈውና በንጉሡ ቀለበት የታተመው ዐዋጅ ሊሻር አይቻልምና።"
\s5
\v 9 በሦስተኛው ወር፥ እርሱም የኒሳን ወር ነው፥ ከወሩም በሃያ ሦስተኛው ቀን በዚያን ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠርተው ነበር። ዐዋጁም አይሁድን በሚመለከት መርዶክዮስ ያዘዘው ሁሉ ተካትቶ ተጽፎበት ነበር። ለየአውራጃው አስተዳዳሪዎች ተጽፎ ነበር፥ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ለሚዋሰኑት 127 የአውራጃ አስተዳዳሪዎችና አለቆች፥ ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሑፍና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ፥ ደግሞም ለአይሁድ በራሳቸው ጽሑፍና ቋንቋ ተጻፈ።
\s5
\v 10 መርዶክዮስ በንጉሥ አርጤክስስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም አተመው። ደብዳቤዎቹንም ለንጉሡ አገልግሎት በሚውሉና ለዚሁ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልዕክተኞች ላከው።
\v 11 በየከተማው ያሉ አይሁዶች በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡና ሕይወታቸውን እንዲከላከሉ፤ ልጆችንም ሆነ ሴቶችን ጨምሮ ከየትኛውም ሕዝብም ሆነ አውራጃ እነርሱን ለማጥቃት መሣሪያ የሚያነሣውን ኃይል ሁሉ እንዲያጠፉ፥ እንዲገድሉና እንዲደመስሱ ንብረታቸውንም እንዲበዘብዙ ንጉሡ ፈቃድ ሰጣቸው።
\v 12 ይህ በንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ በአሥራ ሁለተኛው ወር፥ እርሱም አዳር የሚባለው ወር ነው፥ በአሥራ ሦስተኛው ቀን ተግባራዊ የሚደረግ ነበር።
\s5
\v 13 የዐዋጁ ቅጅ ሕግ ሆኖ በመውጣት ሕዝብ ሁሉ እንዲያውቀው ተደረገ። አይሁድ በዚያን ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁዎች መሆን ነበረባቸው።
\v 14 ስለዚህ መልዕክተኞቹ ለንጉሡ አገልግሎት በሚውሉ የቤተመንግሥት ፈረሶች ላይ ተቀመጡባቸው። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ። ደግሞም የንጉሡ ዐዋጅ ከሱሳ ቤተመንግሥት ተነገረ።
\s5
\v 15 ከዚያም መርዶክዮስ ንጭና ሰማያዊ የክብር ልብስ ለብሶ፥ ታላቅ የወርቅ አክሊልም ደፍቶ፥ ከሐምራዊና ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ መጎናጸፊያ ደርቦ ከንጉሡ ፊት ወጣ። የሱሳ ከተማም ደስ አላት፥ እልልም አለች።
\v 16 ለአይሁድም ብርሃንና ፈንጠዚያ፥ ደስታና ክብር ሆነላቸው።
\v 17 የንጉሡ ዐዋጅ በደረሰበት ሁሉ፥ በየአውራጃውና በየከተማው በአይሁድ መካከል ደስታና ፈንጠዚያ፥ ግብዣና በዓል ሆነ። አይሁድን መፍራት በላያቸው ላይ ወድቆ ስለነበረ በምድሩ ከሚኖሩ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ብዙዎቹ አይሁድ ሆኑ።
\s5
\c 9
\p
\v 1 አዳር ተብሎ በሚጠራው በአሥራ ሁለተኛው ወር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ቀን የንጉሡ ሕግና ዐዋጅ ተግባራዊ በሚደረግበት፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊያጠፏቸው ተስፋ ባደረጉበት ቀን ነገሩ ተቀየረ። አይሁዶች በሚጠሏቸው ላይ የበላይነትን አገኙ።
\v 2 አይሁድ ሊያጠፏቸው በሞከሩት ላይ እጆቻቸውን ለማንሣት ከንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ ወደ ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። እነርሱን መፍራት በሕዝብ ሁሉ ላይ ወድቆ ስለነበረ ማንም ሊቃወማቸው አልቻለም።
\s5
\v 3 የአውራጃዎቹ አለቆች፥ የአውራጃ ገዢዎች፥ መኳንንቶችና የንጉሡ አስተዳዳሪዎች መርዶክዮስን በመፍራት ተይዘው ስለነበር አይሁድን አገዟቸው።
\v 4 መርዶክዮስ በንጉሡ ቤት ታላቅ ነበር፥ ዝናውም በአውራጃዎቹ ሁሉ ተሰራጨ፥ መርዶክዮስ የተባለውም ሰው ታላቅ ሆነ።
\v 5 አይሁድም ጠላቶቻቸውን በሰይፍ አጠቋቸው፥ ገደሏቸው፥ አጠፏቸውም፥ በእነዚያ ይጠሏቸው በነበሩት ላይ ደስ ያሰኛቸውን አደረጉባቸው።
\s5
\v 6 አይሁድ በራሱ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችን ገደሉ፥ አጠፉም።
\v 7 የአይሁድ ጠላት የሐመዳቱን ልጅ
\v 8 የሐማን አሥሩን ወንዶች ልጆቱን፥ ፓርሻንዳታን፥ ደልፎንን፥ አስፓታን፥
\v 9 ፖራታን፥ አዳልያን፥ አሪዳታን፥
\v 10 ፓርማሽታን፥ አሪሳይን፥ አሪዳይንና ዋይዛታን ገደሉ። ነገር ግን ምንም ዝርፊያ አልፈጸሙም።
\s5
\v 11 በተመሸገችው ከተማ፥ በሱሳ፥ በዚያን ቀን የተገደሉት ሰዎች ብዛት ለንጉሡ ተነገረው።
\v 12 ንጉሡም ንግሥት አስቴርን፥ "አይሁድ አሥሩን የሐማ ወንዶች ልጆች ጨምሮ በሱሳ ከተማ ውስጥ አምስት መቶ ሰዎችን ገደሉ። በቀሩት የንጉሡ አውራጃዎች ምን አድርገው ይሆን? አሁን የምትለምኚው ምንድነው? እርሱም ይሰጥሻል። የምትጠይቂውስ ምንድነው? እርሱም ይደረግልሻል" አላት።
\s5
\v 13 አስቴርም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ፥ በሱሳ የሚገኙ አይሁዶች ዛሬ ያደረጉትን ነገም ደግሞ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸው፥ አሥሩ የሐማ ልጆች ሬሳም በመስቀያ ይሰቀል" አለችው።
\v 14 ስለዚህ ንጉሡ ይህ እንዲፈጸም አዘዘ። ዐዋጁም በሱሳ ተሰራጨ፥ አሥሩን የሐማ ወንዶች ልጆች ሰቀሏቸው።
\s5
\v 15 በአዳር ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በሱሳ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ አንድ ላይ ተሰብስበው ሦስት መቶ ተጨማሪ ሰዎችን ገደሉ፥ እጆቻቸውን ግን ለመበዝበዝ አልዘረጉም።
\v 16 በንጉሡ አውራጃዎች ይኖሩ የነበሩት፥ የቀሩት አይሁድ ሕይወታቸውን ለመከላከል በአንድ ላይ ተሰባሰቡ፥ ይጠሏቸው የነበሩትን ሰባ አምስት ሺህ ሰው ገደሉ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ። ነገር ግን ወደ ገደሏቸው ሰዎች ጠቃሚ ቁሳቁስ እጆቻቸውን አልዘረጉም።
\s5
\v 17 በአዳር ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ሆነ፥ በአሥራ አራተኛው ቀን ዐረፉ፥ ቀኑንም የግብዣና የደስታ አደረጉት።
\v 18 በሱሳ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን በአንድ ላይ ተሰባሰቡ። በአሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉት።
\v 19 በገጠር ከተሞች የሚኖሩ የመንደሩ አይሁድ የአዳርን ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የግብዣና የደስታ ቀን አድርገው የሚያከብሩትና እርስ በርሳቸው የምግብ ስጦታ መለዋወጫ ቀን ያደረጉት ለዚህ ነው።
\s5
\v 20 መርዶክዮስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በመጻፍ በንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ለሚኖሩ አይሁዶች በሙሉ በየዓመቱ በአዳር ወር
\v 21 አሥራ አራተኛውንና አሥራ አምስተኛውን ቀን እንዲጠብቁት በማዘዝ ደብዳቤዎችን ጻፈላቸው።
\v 22 እነዚህ ቀናት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ያረፉባቸው፥ ሀዘናቸው ወደ ደስታ፥ ልቅሶአቸውም ወደ ደስታ በዓል የተለወጠባቸው ቀናት ነበሩ። እነርሱም ቀኖቹን የግብዥና የደስታ፥ ለእርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ የሚለዋወጡበት፥ ለድሆችም ስጦታ የሚያበረክቱባቸው መሆን ነበረባቸው።
\s5
\v 23 ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ በጻፈላቸው ደብዳቤ መሠረት የጀመሩትን በዓል ማክበራቸውን ቀጠሉ።
\v 24 በዚያን ጊዜ የአይሁዶች ሁሉ ጠላት፥ የሐመዳቱ ልጅ ሐማ፥ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፥ ሊሰባብርና ሊያፈርሳቸውም ፉር የተባለውን ዕጣ ጥሎ ነበር።
\v 25 ጉዳዩ ወደ ንጉሡ ፊት በቀረበ ጊዜ ግን ሐማ በአይሁድ ላይ ያዘጋጀው ክፉ ዕቅድ በእርሱ በራሱ ላይ እንዲመለስበትና ወንዶች ልጆቹ በስቅላት እንዲቀጡ በደብዳቤ አዘዘ።
\s5
\v 26 ስለዚህ ፉር ከሚለው ስም በመነሣት አነዚህን ቀናት ፉሪም ብለው ጠሯቸው። በዚህ ደብዳቤ በተጻፉት፥ እነርሱም ባዩትና በደረሰባቸው ነገር ምክንያት አይሁድ አዲስ ልማድና አደራረግን ተቀበሉ።
\v 27 ይህም ልማድ ለእነርሱ፥ ለትውልዳቸውና እነርሱን ለተጠጋ ሁሉ የሚቀጥል ነበር። በየዓመቱ እነዚህ ሁለት ቀናት መከበር ነበረባቸው። ቀኖቹንም በየዓመቱ በተመሳሳይ ጊዜ፥ በአንድ ዓይነት መንገድ ማክበር ነበረባቸው። አነዚህ ቀኖች በየትውልዱ፥ በየቤተሰቡ፥ በየአውራጃውና በየከተማው መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል።
\v 28 እነዚህ አይሁዶችና ትውልዶቻቸው እነዚህን የፉሪም ቀናት ፈጽመው እንዳይረሷቸው፥ በታማኝነት መጠበቃቸውንም በፍጹም ማቋረጥ አይኖርባቸውም።
\s5
\v 29 የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ስለ ፉሪም ይህንን ሁለተኛ ደብዳቤ በሙሉ ሥልጣን ጽፈው አጸኑት።
\s5
\v 30 በአርጤክስስ መንግሥት በ127 አውራጃዎች ውስጥ ለሚኖሩ አይሁድ በሙሉ ደኅንነትንና እውነትን የሚመኙላቸው ደብዳቤዎች ተጻፉላቸው።
\v 31 አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር አይሁድን እንዳዘዙት የፉሪም ቀናት በተወሰነላቸው ጊዜያት እንዲደረጉ እነዚህ ደብዳቤዎች አጸኑት። አይሁድ ልክ የጾሙንና የለቅሶውን ጊዜ አንደተቀበሉት ይህንን ትዕዛዝ ደግሞ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ተቀበሉት።
\v 32 ፉሪምን በሚመለከት የአስቴር ትዕዛዝ እነዚህን መመሪያዎች አጸና፥ እርሱም በመጽሐፍ ተጻፈ።
\s5
\c 10
\p
\v 1 ከዚያም ንጉሥ አርጤክስስ እስከ ባህር ጠረፍ ባለው ሀገር ላይ ግብር ጣለ።
\v 2 የኃይሉና የብርታቱ ሥራ ሁሉ፥ ንጉሡ ከፍ ከፍ ካደረገው ከመርዶክዮስ የታላቅነቱ ሙሉ ታሪክ ጋር በፋርስና በሜዶን ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ላይ ተጽፏል።
\s5
\v 3 አይሁዳዊው መርዶክዮስ ከንጉሥ አርጤክስስ ቀጥሎ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር። የሕዝቡን ደኅንነት የፈለገና ስለ ሕዝቡም ሁሉ ሰላም የተናገረ፥ በብዙ አይሁድ ወንድሞቹም የታወቀና በአይሁድ መካከል ታላቅ የሆነ ሰው ነበር።