am_ulb/12-2KI.usfm

1395 lines
204 KiB
Plaintext

\id 2KI
\ide UTF-8
\h 2ተኛ ነገስት
\toc1 2ተኛ ነገስት
\toc2 2ተኛ ነገስት
\toc3 2ki
\mt 2ተኛ ነገስት
\s5
\c 1
\p
\v 1 አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞአብ በአስራኤል ላይ ዐመፀ፡፡
\v 2 በዚያን ጊዜ የአስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ ክፉኛ ቆስሎ ነበር፤ እርሱም እኔ ከዚህ ሕመም እድን እንደሆነ በፍልስጥኤም የአቃሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡል ጠይቁልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፡፡
\s5
\v 3 ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔሌዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ ነውን?
\v 4 ስለዚህ እግዚአብሔር እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም፤ ከተኛህበት አልጋም አትነሣም፤ ብሎሃል በሉት፡፡ ከዚያም ኤልያስ ትቶ ሄደ፡፡
\s5
\v 5 መልእተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ? ሲል ጠየቃቸው፡፡
\v 6 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድን ነው? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም፤ ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም!
\s5
\v 7 ንጉሡም በመንገድ ያገኛችሁት ይህንን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው? ሲል ጠየቃቸው፡፡
\v 8 እነርሱም ጠጉራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው ሲሉ መለሱለት፡፡ ንጉሡም እርሱማ ኤልያስ ነው! አለ፡፡
\s5
\v 9 ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፡፡ መኮንኑም ኤልያስን በአንድ ኮረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡
\v 10 ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡
\s5
\v 11 ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡
\v 12 ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡
\s5
\v 13 ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኮንን ላከ፤ ይህኛው መኮንን ግን ወደ ኮረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን፤ ሕይወትችንንም ከሞት አድን፣
\v 14 ሌሎቹን ሁለት መኮንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ፡፡
\s5
\v 15 የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ አለው፡፡ ስለዚህም ኤልያስ ከመኮንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፡፡
\v 16 እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁ መልእክተኞችን የላክህ በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቁጠርህ ነውን? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ሳትወርድ ትሞታለህ እንጂ አትድንም አለው፡፡
\s5
\v 17 ስለዚህ እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፡፡ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ። ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር፡፡
\v 18 ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
\s5
\c 2
\p
\v 1 እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጉዞ ጀመሩ፡፡
\v 2 በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ እኔ ወደ ቤቴል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ ከቶ ከአንተ አልለይም ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤቴል ሄዱ፡፡
\s5
\v 3 በዚያ የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፣ እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን? ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኤልሳዕም አዎን ዐውቃለሁ፣ ነገር ግን ዝም በሉ ሲል መለሰላቸው፡፡
\v 4 ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ ከቶ ከአንተ አልለይም፣ ሲል መለሰለት፡፡ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ፡፡
\s5
\v 5 በዚህም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን? ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኤልሳዕም አዎን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ ሲል መለሰላቸው፡፡
\v 6 ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን እነሆ አንተ በዚህ ቆይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል አለው፡፡ ኤልሳዕ ግን እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ ከቶ ከአንተ አልለይም፤ ሲል መለሰለት፡፡ እነዚህም አብረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡
\s5
\v 7 ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤
\v 8 ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሸገሩ፡፡
\s5
\v 9 በዚህም ኤልያስ ኤልሳዕን እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ አለው፡፡ ኤልሳዕም ያንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችለኝ መንፈስ በእጥፍ ይሰጠኝ ሲል መለሰለት፡፡
\v 10 ኤልያስም «ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየከውን ስጦታ መቀበል ትችላልህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም» ብሎ መለሰለት፡፡
\s5
\v 11 እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ ፈረሰኞች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ፡፡
\v 12 ኤልሳዕም ይህን ሁሉ እያየ «የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች የሆንከው አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!» እያለ ወደ ኤልያስ ጮኸ፤ ከዚያም በኋላ ኤልያስን ዳግመኛ አላየውም፡፡ ኤልሳዕም ከሐዘን ብዛት የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደ፤
\s5
\v 13 ከኤልያስም የወደቀውን ካባ ከመሬት አነሣ፤ ከዚያም ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ደርቻ ቆመ፡፡
\v 14 ውሃውንም በኤልያስ ካባ መትቶ፣ «የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?» አለ፤ ከዚያም በኋላ እንደገና በመታው ጊዜ ውሃው ወደ ቀኝና ግራ ተከፍሎለት ወደ ማዶ ተሻገረ፡፡
\s5
\v 15 ከኢያሪኮ የመጡት ነቢያት እርሱን ባዩት ጊዜ፣ «በኤልያስ ላይ ዐድሮ የነበረው የመንፈስ ኀይል በኤልሳዕ ላይ አርፏል!» አሉ፤ ወደ እርሱም በመቅረብ ጎንበስ ብለው እጅ ነሡት
\v 16 «እነሆ! በዚህ ጠንካራ የሆንን ኀምሳ ሰዎች አለን፤ እንሂድና ጌታህን እንፈልገው፤ ምናልባት የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወስዶ በአንድ ተራራ ወይም ሸለቆ ውስጥ አሳርፎት ይሆናል፡፡» ኤልሳዕም “አትሂዱ” ሲል መለሰ፡፡
\s5
\v 17 እነርሱ ግን እምቢ በማለት እስኪያፍር ድረስ አጥብቀው ስለ ለመኑት በጉዳዩ ተስማማና ኀምሳ ሰዎች ሄደው ሦስት ቀን ሙሉ ኤልያስን ፈለጉት፤ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡
\v 18 ከዚያም በኋላ በኢያሪኮ ሆኖ ወደሚጠብቃቸው ወደ ኤልሳዕ ተመለሱ፤ ኤልሳዕም «እኔ ቀድሞውንስ አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?» አላቸው፡፡
\s5
\v 19 ጥቂት ሰዎች ከኢያሪኮ ወደ ኤልሳዕ መጥተው «ጌታችን አንተ እንደምታውቀው ይህች ምድር መልካም ናት፤ ውሃው ግን መጥፎ በመሆኑ ምድሪቱ ምርት አትሰጥም፤ ስለሁኔታው እንለምንሃለን» አሉት፡፡
\v 20 ኤልሳዕም «በአዲስ ሳህን ውስጥ ጨው ጨምራችሁ አምጡልኝ» ብሎ አዘዘ፡፡ እነርሱም እንዳዘዛቸው አድርገው አመጡለት፡፡
\s5
\v 21 እርሱም ወደ ምንጩ ሄዶ በውሃ ውስጥ ጨው በመጨመር «እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው ‹እኔ ይህን ውሃ በመፈወስ ንፁህ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የሞትና የምርት መጨንገፍ ምክንያት አይሆንም›» ሲል ተናገረ፡፡
\v 22 ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ኤልሳዕ በተናገረው መሠረት ውሃው እስከ ዛሬ ድረስ ንጹሕ ሆነ፡፡
\s5
\v 23 ኤልሳዕም ወደ ቤቴል ለመሄድ ከኢያሪኮ ተነሣ፡፡ በመንገድ ሳለ ከከተማይቱ በርከት ያሉ ልጆች ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ አንተ ራሰ መላጣ! ራሰ መላጣ! ከዚህ ውጣ እያሉ ጮኹበት፡፡
\v 24 ኤልሳዕም መለስ ብሎ ዙሪያውን በመቃኘት አትኩሮ ተመለከታቸውና በእግዚአብሔር ስም ረገማቸው፤ በዚህም ጊዜ ሁለት እንስት ድቦች ከጫካ ወጥተው ከእነዚያ ልጆች መካከል አርባ ሁለቱን ሰባብረው ጣሉአቸው፡፡
\v 25 ኤልሳዕም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ ዘግየት ብሎ ግን ወደ ሰማርያ ተመለሰ፡፡
\s5
\c 3
\p
\v 1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ እርሱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
\v 2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡ ነገር ግን እንደ አባቱና እናቱ አልነበረም፤ ምክንያቱም በዓል ተብሎ የሚጠራውን አባቱ አሠርቶት የነበረውን በዕድ አምላክ ምስል አስወገደ፡፡
\v 3 ይህም ሆኖ ከእርሱ በፊት እስራኤል ወደ ኃጢአት የመራው የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን አምልኮ ተከተለ እንጂ አላስወገደውም፡፡
\s5
\v 4 የሞአብ ንጉሥ ሞሳ በግ አርቢ ነበር፤ በየዓመቱም አንድ መቶ ሺህ ጠቦት የአንድ መቶ ሺህ በጎች ጠጉር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር፤
\v 5 ነገር ግን የእስራኤል ንጉሥ አካዓብ በሞተ ጊዜ የሞአብ ንጉሥ ሞሳ በእስራኤል ላይ ዐመፀ፡፡
\v 6 በዚያን ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ወዲያውኑ ከሰማርያ ወጥቶ ወታደርቹን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ፤
\s5
\v 7 ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥም የሞአብ ንጉሥ በእኔ ላይ አምፆብኛል፤ በእርሱ ላይ በማደርገው ጦርነት ከእኔ ጋር ትተባበራለህን? የሚል መልእክት ላከ፡፡ ንጉሥ ኢሣፍጥም አዎን እተባበርሃለሁ፤ እኔን እንደ ራስህ፣ ሠራዊቴን እንደ ሠራዊትህ፣፣ ፈረሶቼንም እንደ ፈረሶችህ መቁጠር ትችላለህ ሲል መለሰለት፡፡
\v 8 እርሱም ልናጠቃ የምንችለው በየትኛው መንገድ ነው? ሲል ጠየቀው፡፡ ንጉሥ ኢዮራምም በኤዶም በረሓ የሚገኘውን ዙሪያ መንገድ ይዘን እንጓዛለን ሲል መለሰለት፡፡
\s5
\v 9 ስለዚህም ንጉሥ ኢዮራም፣ እንዲሁም የይሁዳና የኤዶም ነገሥታት ለዘመቻ ወጡ፤ ከሰባት ቀን ጉዞም በኋላ ውሃ አለቀባቸው፤ ለሠራዊቱም ሆነ ለጭነት እንስሶቻቸው ምንም ውሃ አልነበረም፡፡
\v 10 የእስራኤል ንጉሥ ይህ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን? ወዮልን ሲል ጮኸ፡፡
\s5
\v 11 ንጉሥ ኢዮሣፍጥም በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንድንችል በዚህ አንድ ነቢይ የለም? ሲል ጠየቀ፡፡ ከንጉሥ ኢዮራም ሠራዊት አዛዦች አንዱ፣ ቀድሞ የኤልያስ ረዳት የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ ሲል መልስ ሰጠ፡፡
\v 12 ንጉሥ ኢዮሣፍጥም የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል አለ፤ ከዚያም በኋላ ሦስቱም ነገሥታት ወደ ኤልሳዕ ሄዱ፡፡
\s5
\v 13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ ኢዮራምን እኔ ለአንተ ማድረግ የሚገባኝ ምንድን ነው? ወደ አባትህና እናትህ ነቢያት ሂድ። ንጉሥ ኢዮራምም መልሶ አይደለም፣ ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ለመስጠት የጠራን እግዚአብሔር ነው አለ፡፡
\v 14 ኤልሳዕም እኔ በማገልግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ አንተን ለመርዳት ለመጣው ለይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ስል ነው እንጂ ለአንተስ ምንም ነገር ላደርግልህ ባልተገባ ነበር፡፡
\s5
\v 15 ነገር ግን በገና የሚደረድር ሰው አምጡልኝ አለ፡፡ ባለ በገናውም በሚደረድርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል በኤልሳዕ ላይ ወርዶ እንዲህ አለ፡፡
\v 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በዚህ የደረቀ ሸለቆ ሁሉ የውሃ ጉድጓድ ቆፍሩ፡፡
\v 17 ምንም ዝናብና ነፋስ ባታዩም ይህ ሸለቆ በውሃ የተሞላ ይሆናል፡፡ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና የጭነት እንስሶቻችሁ ሁሉ የምትጠጡት በቂ ውሃ ታገኛላችሁ፡፡
\s5
\v 18 ነገር ግን ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀላል ነገር ነው፡፡ ከዚህ በላይ እርሱ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጎናጽፋችኋል፡፡
\v 19 የተመሸጉና ምርጥ የሆኑ ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል አድርጋችሁ ትይዛላችሁ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቆርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን ትደፍናላችሁ፤ ለም የሆኑ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በማበላሸት ድንጋይ ትከምሩባቸዋላችሁ፡፡
\s5
\v 20 በማግስቱም ጠዋት መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ከኤዶም በኩል የውሃ ምንጭ ፈልቆ ምድሩን ሸፈነው፡፡
\s5
\v 21 ሞአባውያንም ሦስቱ ነገሥታት አደጋ ሊጥሉባቸው መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ፣ ከሽማግሌ እስከ ወጣት መሣሪያ መያዝ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው ወጥተው ለጦርነት መጡ፡፡
\v 22 በማግስቱም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ በውሃው ላይ የሚያበራው የፀሐይ ነጸብራቅ እንደ ደም ቀይ መስሎ ታያቸው፡፡
\v 23 ስለዚህም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ፣ ይህ ነገር ደም ነው፤ የሦስቱ ጠላቶቻችን ሠራዊቶች እርስ በርሳቸው በመተራረድ ተላልቀዋል፤ እንግዲህ ሄደን ሰፈራቸውን እንዝረፍ ተባባሉ፡፡
\s5
\v 24 እነርሱ ወደ ሰፈር በደረሱ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው አደጋ በመጣል ወደ ኋላ መለሱአቸው፤ እስራኤላውያን አገሪቱን ወርረው ሞአባውያንን ጨፈጨፉአቸው፡፡
\v 25 ከተሞቻቸውን ደመሰሱ፤ ለም በሆነው እርሻ ውስጥ በሚያልፉበትም ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውርበት ስለ ነበር በመጨረሻ እርሻዎቹ ሁሉ በድንጋይ ተሸፈኑ፤ ምንጮቻቸውን ደፈኑ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውንም ሁሉ ቆረጡ፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረችው ቂርሔሬስ ብቻ ቀረች፤ እርስዋንም ድንጋይ የሚወነጭፉ ጦረኞች ከበው አደጋ ጣሉባት፡፡
\s5
\v 26 የሞአብ ንጉሥ ድል እንደ ተመታ ባረጋገጠ ጊዜ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎችን እስከትሎ የጠላት ጦር የተሰለፈበትን መስመር ጥሶ ለማምለጥና ወደ ሶሪያ ንጉሥ ለመሄድ ቢሞክርም ከቶ አልተሳካለትም፡፡
\v 27 ስለዚህ በእርሱ ምትክ መንገሥ የሚገባውን የመጀመሪያ ልጁን በከተማይቱ ግንብ ላይ ለሞአብ አምላክ መሥዋዕት አደርጎ አቀረበ፡፡ ስለዚህ በእስራኤል ዘንድ ከፍ ያለ ቁጣ ነበር፡፡ እስራኤላውያንም ለሞአብ ንጉሥ ከተማይቱን ለቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡
\s5
\c 4
\p
\v 1 የነቢያት ጉባኤ አባል የነበረ፣ ባልዋ የሞተባት አንዲት ሴት ወደ ኤልሳዕ መጥታ፣ ጌታዬ ሆይ፣ ባሌ ሞቶብኛል፤ እርሱም አንተ እንደምታውቀው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን እነሆ ለባሌ ገንዘብ አበድሮት የነበረ አንድ ሰው በባሌ ዕዳ ፈንታ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ወስዶ ባሪያ አደርጎ ሊገዛቸው ፈልጎአል አለችው፡፡
\v 2 ኤልሳዕም ታዲያ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለሽ ንገሪኝ? ሲል ጠየቃት፡፡ እርስዋም በትንሽ ማሰሮ ከሚገኝ የወይራ ዘይት በቀር ሌላ ምንም የለኝም ስትል መለሰችለት፡፡
\s5
\v 3 ኤልሳዕም እንዲህ አላት፡- ወደ ጎረቤቶችሽ ሄደሽ ማግኘት የምትችዪውን ያህል ባዶ ማድጋ ለምኚ፤
\v 4 ከዚህም በኋላ አንቺና ልጆችሽ ቤት ገብታችሁ በሩን ዝጉ፡፡ የማሰሮውንም ዘይት ወደ ማድጋዎቹ ማንቆርቆር ጀምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ በሚሞላበት ጊዜ ለብቻው በማግለል አኑሩት፡፡
\s5
\v 5 ስለዚህም ሴትዮዋ ወደ ቤትዋ ሄዳ ከልጆችዋ ጋር በሩን ዘጋች፤ ዘይት የነበረበትን ትንሽ ማሰሮ አንሥታም ልጆችዋ እያቀረቡላት በማንቆርቆር በየማድጋዎቹ ሞላች፡፡
\v 6 ማድጋዎቹንም ሁሉ ከሞሉ በኋላ ሌላ ትርፍ የለም ወይ ስትል ጠየቀች፤ ከልጆችዋም አንዱ ሌላ ማድጋ የለም ሲል መለሰላት፡፡ ከዚያ በኋላ ዘይቱ መውረዱን አቆመ፡፡
\s5
\v 7 እርስዋም ተመልሳ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ሄደች፤ እርሱም እንግዲህ ዘይቱን ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈይ፤ ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ የሚሆንም ብዙ ገንዘብ ይተርፍሻል አላት፡፡
\s5
\v 8 አንድ ቀን ኤልሳዕ አንዲት ሀብታም ሴት ወደምትኖርበት ወደ ሱነም ሄደ፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ ጋበዘችው፤ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ወደ ሱነም በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ በቤትዋ ይመገብ ነበር፡፡
\v 9 እርስዋም ባልዋን እንዲህ አለችው፤ ብዙ ጊዜ ወደ ቤታችን የሚመጣው ይህ ሰው የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሰው ስለ መሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡
\s5
\v 10 ስለዚህም በሰገነቱ ላይ አንድ ትንሽ ክፍል ሠርተን በዚያች ውስጥ አል፣ ጠረጳዛ፣ ወንበርና የፋኖስ መብራት እናኑርለት፤ እርሱም ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ እዚያ ያርፋል፡፡
\v 11 አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደዚያ እንደገና ሄደ፤ ወደ ተሠራለት ክፍል ገብቶ እረፍት አደረገ፡፡
\s5
\v 12 ኤልሳዕም ለአገልጋዩ ግያዝ እንዲህ አለ፡- «ይህችን ሱናማዊት ጥራት» በጠራትም ጊዜ መጥታ በፊቱ ቆመች፡፡
\v 13 ኤልሳዕም ግያዝን እንዲነግራት እንዲህ አለው፡- «እኛን ለመንከባከብ ይህን ሁሉ ተቸገረሽ፤ እኛ ደግሞ ለአንቺ ምን እናድርግልሽ? ለንጉሥ ወይም ለጦር አዛዥ ስለ አንቺ ልንነግርልሽ እንችላለን? በላት አለው፡፡ እርስዋም «በዘመዶቼ መካከል ስለምኖር በዚህ ስፍራ ምንም የሚቸግረኝ ነገር የለም» ስትል መለሰችለት፡፡
\s5
\v 14 ኤልሳዕም ግያዝን «ታዲያ ምን ልናደርግላት እችላለን?» ሲል ጠየቀው፡፡ ግያዝም “እነሆ ልጅ የላትም፣ ባሏም ሸምግሎአል” አለ፡፡
\v 15 ኤልሳዕም ጥራት አለው፡፡ ሲጠራትም መጥታ በበሩ አጠገብ ቆመች፡፡
\v 16 ኤልሳዕም አላት፡- በመጪው ዓመት በዚህ ጊዜ ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ አላት፡፡ እርስዋም ጌታዬ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! እባክህ አገልጋይህን አትዋሻት አለችው፡፡
\s5
\v 17 ሴቲቱም ፀነሰች፤ ልክ ኤልሳዕ የተናገረው ጊዜ ሲደርስ በዓመቱ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡
\v 18 ሕፃኑም በአደገ ጊዜ አንድ ቀን አባቱ ከአጫጆች ጋር ወዳለበት ሄደ፡፡
\v 19 እርሱም በድንገት “ራሴን! ራሴን!” ብሎ ወደ አባቱ ጮኸ፡፡ አባትየውም አንዱን አገልጋይ ጠርቶ፡- “ልጁን ወደ እናቱ ውሰድ” ሲል አዘዘው፡፡
\v 20 አገልጋዩም ልጁን ተሸክሞ ወደ እናቱ ባመጣው ጊዜ እርስዋም ተቀብላው በጉልበትዋ እንደታቀፈችው ቆይቶ እኩለ ቀን ላይ ሞተ፡፡
\s5
\v 21 ሴቲቱም ተነሥታ ልጁን በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አስተኝታ በሩን ዘግታበት ተመልሳ ሄደች፡፡
\v 22 ባልዋንም ጠርታ “አንድ አገልጋይና አንድ አህያ ላክልኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ሰው ዘንድ ሄጄ እመለሳለሁ አለችው፡፡
\s5
\v 23 ባልዋ “ለምን መሄድ ትፈልጊያለሽ? ዛሬ ሰንበት ወይም የጨረቃ በዓል የሚከበርበት ቀን አይደለም” አላት፡፡ እርስዋም “ግድ የለም፤ እንዳልኩህ አድርግ” አለችው፡፡
\v 24 እርስዋም አህያው እንዲጫንላት ካደረገች በኋላ አገልጋዩን “በተቻለ መጠን አህያው እንዲፈጥን አድርግ፤ እኔም ካልነገርኩህ በቀር ቀስ ብሎ እንዲሄድ ዕድል አትስጠው” ስትል አዘዘችው፡፡
\s5
\v 25 እርስዋም ከዚያ ተነሥታ ኤልሳዕ ወደነበረበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣች፡፡ የእግዚአብሔርም ሰው ገና በሩቅ ሳለች ወደ እርሱ ስትመጣ አይቶ አገልጋዩን ግያዝን «ተመልከት! ያቺ ሱነማዊት ወደዚህ እየመጣች ነው! አለው፡፡
\v 26 ፈጠን ብለህ ሂድና የእርስዋን፤ የባልዋንና የልጅዋን ደኅንነት ጠይቃት» አለው፡፡ እርስዋም ግያዝን «ሁላችንም ደኅና ነን» ስትል ነገረችው፡፡
\s5
\v 27 ወደ ኤልሳዕ ወደ ተራራው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ያዘች፤ በዚህ ጊዜ ግያዝ ሊያርቃት ፈለገ፤ ኤልሳዕ ግን «ተዋት፤ እርስዋ ተጨንቃለች፣ እግዚአብሔርም ከእኔ ሰውሮታልና ምንም የነገረኝ ነገር የለም» አለው፡፡
\s5
\v 28 ሴቲቱም «ጌታዬ፣ ልጅ እንድትሰጠኝ ጠይቄህ ነበርን? ‹አታሳስተኝ› ብዬ ነግሬህ አልነበረምን?» አለችው፡፡
\v 29 ኤልሳዕም ግያዝን አለው፡- «ለጉዞ በፍጥነት ተነሣና ምርኩዜን በእጅህ ያዝ፡፡ ወደ ቤትዋ ሂድ፡፡ በመንገድ ማንንም ብታገኝ ሰላምታ አትስጥ፤ ማንም ሰላምታ ቢሰጥህ መልስ አትስጥ፡፡ ምርኩዜን በልጁ ፊት ላይ አኑር!» አለው፡፡
\s5
\v 30 የልጁ እናት ግን ኤልሳዕን «በምትተማመንበት በሕያው እግዚአብሔር ስምና በነፍስህ እምላለሁ፤ ከቶ አንተን ትቼ አልሄድም!» አለችው፤ ስለዚህ እርስዋን ተከትሎ ለመሄድ ተነሣ፤
\v 31 ግያዝም ወደ ፊት ቀድሞአቸው የኤልሳዕን ምርኩዝ በልጁ ፊት ላይ አኖረ፤ ነገር ግን ልጁ ግን አልተናገረም፣ አልሰማም፡፡ ስለዚህም ተመልሶ ሄዶ ኤልሳዕን «ልጁ አልተነሣም» አለው፡፡
\s5
\v 32 ኤልሳዕም ወደ ቤቱ በደረሰ ጊዜ ልጁ ሞቶ አልጋ ላይ ነበር፡፡
\v 33 ስለዚህ ኤልሳዕ ገባና በሩን በልጁና በራሱ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡
\v 34 ሄዶም በልጁ ላይ ተጋደመ፤ አፉን በአፉ ላይ፣ ዐይኖቹን በአይኖቹ ላይ፣ እጆቹን በእጆቹ ላይ አደረገ፤ ራሱን በልጁ ላይ ዘርግቶ ተጋደመ፤ የልጁም ሰውነት መሞቅ ጀመረ፡፡
\s5
\v 35 ከዚያም፣ ኤልሳዕ ተነሥቶ በክፍሉ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ጀመር፤ እንደገናም ተመለሰና በመዘርጋት በልጁ ላይ ተጋደመ፡፡ ልጁም ሰባት ጊዜ ካስነጠሰው በኋላ ዐይኖቹን ከፈተ፡፡
\v 36 ስለዚህ ኤልሳዕ ግያዝን ጠርቶ እንዲህ አለ፣ ሱነማይቱን ጥራት አለው፡፡ እርሱም ጠራት፣ እርስዋም በመጣች ጊዜ ኤልሳዕ ልጅሽ ይኸውልሽ አንሽው አላት፡፡
\v 37 እርስዋ ወደ መሬት ለጥ ብላ በኤልሳዕ ጫማ ላይ በመውደቅ እጅ ነሣች፤ ከዚያም በኋላ ልጅዋን ይዛ ሄደች፡፡
\s5
\v 38 ከዚያም ኤልሳዕ ወደ ጌልጌላ መጣ፡፡ በአገሪቱ ራብ በነበረበት ጊዜ የነቢያት ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፡፡ እርሱም አገልጋዩን እንዲህ አለው፡- ትልቅ ድስት ጥደህ ለነቢያቱ ልጆች ወጥ ሥራላቸው አለው፡፡
\v 39 ከነቢያቱም አንዱ ቅጠላ ቅጠል ለመልቀም ወደ ሜዳ ሄደ፡፡ እርሱም በጫካ ውስጥ የበቀለ የቅል ሐረግ አገኘ፤ መሸከም የሚችለውን ያህል በርከት ያለ ቅል ቆርጦ አመጣ፡፡ እርሱም ከተፈውና ወጡ ውስጥ ጨመረው፤ ነገር ግን ምን እንደሆነ ዐላወቁም፡፡
\s5
\v 40 እነርሱም ወጡን ለሰዎቹ እንዲመገቡት አወጡ፡፡ በኋላም እየበሉ ሳለ ጮኸው፣ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ በድስቱ ውስጥ ሞት አለ! አሉት፤ ስለዚህም ሊበሉት አልቻሉም፡፡
\v 41 ነገር ግን ኤልሳዕ እንዲህ አለ፡- ጥቂት ዱቄት አምጡልኝ፡፡ ያመጡትን ዱቄት በድስቱ ውስጥ ጨምሮ እንዲህ አለ፡- ለሰዎች እንዲበሉ ወጡን አውጡ፡፡ ከዚያ በወጡ ውስጥ የሚጎዳ ነገር አልተገኘም፡፡
\s5
\v 42 በዓል ሻሊሻ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ሰው መጥቶ በመከር ጊዜ በመጀመሪያ ከተወቃው ሃያ የገብስ የዳቦ ሙልሙሎችና አዲስ የተቆረጠ እሸት በከረጢቱ አመጣለት፡፡ እርሱም ይህን እንዲበሉ ለነቢያት ልጆች ስጡአቸው አለ፡፡
\v 43 አገልጋዩም እንዲህ አለ፡- በመቶ ሰዎች ፊት ይህን ምን ብዬ ማቅረብ አለብኝ? ነገር ግን ኤልሳዕ አለ፡- እንዲበሉ ለሰዎቹ ስጣቸው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ይበላሉ ያተርፉማል፡፡
\v 44 ስለዚህም አገልጋዩ ምግቡን አቀረበላቸው፣ እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ የተረፈ ምግብ ነበር፡፡
\s5
\c 5
\p
\v 1 የሶርያ ጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን በሶርያ ንጉሥ ዘንድ ታላቅና የተከበረ ነበር፤ ምክንያቱም በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር ለሶርያ ሠራዊት ድልን አጎናጽፎ ነበር፡፡ እርሱም ደግሞ ጠንከራና ብርቱ ሰው ነበር፤ ነገር ግን ለምጻም ነበር፡፡
\v 2 ሶርያውያን በእስራኤላውያን ላይ ወረራ በፈጸሙበት ጊዜ አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ ማርከው ወስደው ነበር፤ እርስዋም ለንዕማን ሚስት ሠራተኛ ሆና ታገለግል ነበር፡፡
\s5
\v 3 ልጃገረዲቱም እመቤትዋን እንዲህ አለቻት፡- «ጌታዬ በሰማርያ ወደሚገኘው ነቢይ ቢሄድ እወዳለሁ! እርሱም ጌታዬን ከዚህ ለምጽ ሊያነፃው ይችላል!» አለቻት፡፡
\v 4 ንዕማንም ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ልጃገረዲቱ ያለችውን ሁሉ ነገረው፡፡
\s5
\v 5 ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ እንዲህ አለ፣ «ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ፤ አሁን አንተ ሂድ» ብሎ ፈቀደለት፡፡ ንዕማንም ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ መሐለቅ ወርቅና ዐሥር መለወጫ ልብስ አስጭኖ፣ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
\v 6 እርሱም ለእስራኤል ንጉሥ የተጻፈለትን ደብዳቤ ወሰደ፣ ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፡- «ይህ ደብዳቤ የኔ አገልጋይ ስለሆነው ስለ ንዕማን ጉዳይ የሚገልጥ ነው፤ ከለምጹም እንድትፈውሰው ወደ አንተ ልኬዋለሁ» የሚል ነበር፡፡
\s5
\v 7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ በቁጣ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፡- «የሶሪያ ንጉሥ ይህን ሰው እንድፈውስለት እንዴት ይገምታል? እኔ ሰውን ከለምጽ እፈውስ ዘንድ የማዳንና የመግደል ሥልጣን ያለኝ እግዚአብሔር መሰልኩትን? ይህ አባባል ከእኔ ጋር ጠብ ለመጀመር የፈለገ ይመስላል!» አለ፡፡
\s5
\v 8 ስለዚህ የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ ወደ ንጉሡ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፡- «ስለምን ልብስህን ቀደድክ? ሰውየውን ወደ እኔ ላከው፤ እርሱም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል!» አለው፡፡
\v 9 ስለዚህም ንዕማን ከፈረሶችና ከሠረገላዎቹ ጋር ወደ ኤልሳዕ ቤት መጥቶ በር ላይ ቆመ፡፡
\v 10 ኤልሳዕም አንዱን አገልጋይ ልኮ «ሄደህ በዮርዳኖስ ወንዝ ሰባት ጊዜ ራስህን በማጥለቅ ታጠብ፤ ሰውነትህም ይመለሳል፤ ንጹሕም ትሆናለህ› ብለህ ለዚህ ሰው ንገረው» ሲል ተናገረው፡፡
\s5
\v 11 ንዕማን ግን ተቆጥቶ ለመመለስ ተነሣ፤ እንዲህም አለ፡- “እኔ ነቢዩ መጥቶ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በሽታዬ ያለበትን ቦታ በእጆቹ በመዳሰስ ከለምጽ በሽታዬ ይፈውሰኛል ብዬ ነበር፡፡
\v 12 በእስራኤል ከሚገኙት ወንዞች ይልቅ በአገሬ በደማስቆ የሚገኙት አባናና ፋርፋ አይሻሉምን? በእነርሱ ታጥቤ ንጹሕ መሆን አልችልምን?” ስለዚህ ተነሥቶ ሄደ፡፡›
\s5
\v 13 የንዕማንም አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው፡- «ጌታችን ሆይ፣ ነቢዩ ሌላ ከባድ ነገር እንድታደርግ ቢያዝህ ኖሮ ትፈፅመው ነበር፤ ታዲያ ነቢዩ ባዘዘህ መሠረት ታጥበህ ከበሽታህ መንጻት ምን ይከብድሃል?» አሉት፡፡
\v 14 ከዚያም ንዕማን የእግዚአብሔር ሰው ባዘዘው መሠረት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ ሰባት ጊዜ በመነከር ታጠበ፤ ከበሽታውም ፈጽሞ ነጻ፡፡ ሰውነቱም እንደ ሕፃን ልጅ ገላ በመታደስ ፍፁም ጤናማ ሆነ፡፡
\s5
\v 15 ንዕማንና አጃቢዎቹ ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሰው መጥተው በፊቱ ቆሙ፡፡ ንዕማንም እንዲህ አለ፡- «ከእስራኤል አምላክ በቀር በምድር ላይ ሌላ አምላክ እንደሌለ እነሆ አሁን ዐወቅሁ፡፡ ስለዚህም ከአገልጋይ ይህን ስጦታ እባክህ ተቀበለኝ» አለው፡፡
\v 16 ኤልሳዕ ግን «በፊቱ ቆሜ በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ምንም ስጦታ አልቀበልህም» ሲል መለሰለት፡፡ ንዕማንም ስጦታውን እንዲቀበል አጥብቆ ቢለምነውም ኤልሳዕ ሊቀበለው አልፈቀደም፡፡
\s5
\v 17 ስለዚህም ንዕማን እንዲህ አለ፡- «ስጦታዬን የማትቀበለኝ ከሆነ ለሌሎች ባዕዳን አማልክት የሚቃጠልም ሆነ ሌላ አይነት መሥዋዕት የማቀርበውን ከአሁን ጀምሮ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ለማቅረብ ስለወሰንሁ የሁለት በቅሎ ጭነት አፈር ይዤ እንድሄድ ፍቀድልኝ፡፡»
\v 18 ስለዚህም የአገሬን ንጉሥ በማጀብ ሬሞን የተባለ ባዕድ አምላክ ወደሚመለክበት መቅደስ ብገባና ብሰግድም እንኳ እግዚአብሔር በዚህ ጉዳይ ይቅር እንደሚለኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በእርግጥም በዚህ ጉዳይ ይቅር ይለኛል፡፡»
\v 19 ኤልሳዕም «በሰላም ሂድ!» አለው፤ ንዕማንም ተሰናብቶ ሄደ፡፡
\s5
\v 20 እርሱም ጥቂት ራቅ ብሎ እንደ ሄደ፣ የኤልሳዕ አገልጋይ ግያዝ ለራሱ እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ ሶሪያዊው ንዕማን ካመጣው ስጦታ ሳይቀበል አሰናብቶታል፡፡ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፣ ተከትዬው ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ» ሲል በልቡ አሰበ፡፡
\v 21 ስለዚህም ግያዝ ንዕማንን ከኋላው ተከተለው፡፡ ንዕማንም መለስ ብሎ አንድ ሰው እየሮጠ ሲከተለው ባየ ጊዜ እርሱን ለመገናኘት ከሠረገላው ወርዶ እንዲህ አለ፡- «ሁሉ ነገር ሰላም ነው?»
\v 22 ግያዝም፡- «ሁሉ ነገር መልካም ነው፡፡ ጌታዬ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖሩ ሁለት ወጣት የነቢያት ልጆች ድንገት መጡብኝ፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መቀየሪያ ልብሶች ላክልኝ ብሎ ልኮኛል» ሲል መለሰለት፡፡
\s5
\v 23 ንዕማንም፡- «እባክህ ሁለት መክሊት ብር ለመስጠት በጣም ደስተኛ ነኝ» ሲል መለሰለት፡፡ ብሩን በሁለት ከረጢት ሞልቶ ከሁለት መለወጫ ልብሶች ጋር በሁለት አገልጋዮች አስይዞ ከግያዝ ፊት እንዲሄዱ አደረገ፡፡
\v 24 ግያዝም ወደ ኮረብታው በደረሰ ጊዜ፣ ግያዝ ሁለቱን ከረጢት ብር ከእጃቸው ወስዶ ወደ ቤት አስገባ፡፡ እነርሱንም አሰናብቶአቸው ሄዱ፡፡
\v 25 ወደ ቤት ተመልሶ ገብቶ በጌታው በኤልሳዕ ፊት በቆመ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ አለው፡- «ግያዝ ከወዴት መጣህ?» እርሱም፡- «ጌታዬ፣ አገልጋይህ የትም አልሄድኩም» ሲል መለሰ፡፡
\s5
\v 26 ኤልሳዕም ለግያዝ፡- «ሰውየው አንተን ለመገናኘት ከሠረገላው ሲወርድ እኔ በመንፈስ ከአንተ ጋር አልነበርኩምን? እነሆ አሁን ገንዘብና ልብስ፣ የወይራና የወይን ተክል ቦታ፣ በግና የቀንድ ከብት ወይም አገልጋዮችን ለመቀበል ጊዜው ነውን?
\v 27 ስለዚህ እነሆ የንዕማን ለምጽ ወደ አንተና ዘሮችህ ለዘላለም ይተላለፋል» አለው፡፡ ግያዝም ከፊቱ ወጥቶ ሄደ፣ ለምጹም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡
\s5
\c 6
\p
\v 1 የነቢያት ልጆችም ኤልሳዕን፡- «ከአንተ ጋር የምንኖርበት ስፍራ ከሁላችንም ጠባብ ነው አሉት፡፡
\v 2 ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደን ዛፍ ቆርጠን የምንኖርበትን ቤት በዚያ እንድንሠራ ፍቀድልን!» አሉት፡፡ ኤልሳዕም «መልካም ነው ቀጥሉ!» በማለት መለሰላቸው፡፡
\v 3 ከእነርሱም አንዱ ኤልሳዕን አብሮአቸው እንዲሄድ ጠየቀው፤ ኤልሳዕም እሄዳለሁ አላቸው፡፡
\s5
\v 4 እርሱም አብሮአቸው ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ ዛፍ የመቁረጥ ተግባራቸውን ጀመሩ፡፡
\v 5 ነገር ግን አንዱ ዛፍ በመቁረጥ ላይ ሳለ መጥረቢያው ወድቆ ውሃው ውስጥ ጠለቀ፤ እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ: - «ጌታዬ ሆይ! መጥረቢያው የተዋስኩት ነው፣ ምን አደርጋለሁ?» ሲል ጮኸ፡፡
\s5
\v 6 የእግዚአብሔርም ሰው፡- «በየት በኩል ነው የወደቀው?» ሲል ጠየቀው፡፡ ሰውየውም መጥረቢያው የወደቀበትን ስፍራ አሳየው፡፡ እርሱም አንድ እንጨት ቆርጦ ወደ ውሃው በጣለ ጊዜ መጥረቢያው ተንሳፈፈ፡፡
\v 7 ኤልሳዕም፡- «ውሰደው» አለው፡፡ ሰውየውም ጎንበስ ብሎ አነሣው፡፡
\s5
\v 8 እነሆ፣ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከፍቶ ነበር፡፡ እርሱም ከጦር አዛዦቹ ጋር ተማክሮ የሚሰፍሩበትን ቦታ መረጠ፡፡
\v 9 የእግዚአብሔርም ሰው: - «ሶርያውያን ደፈጣ አድርገው ስለሚጠብቁህ ከዚህ ወደዚያ ስፍራ አትቅረብ» ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ፡፡
\s5
\v 10 የእስራኤልም ንጉሥ ወታደሮቹ ወደሚኖሩበት፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደተናገረበትና ወዳስጠነቀቀበት ስፍራ ላከ፡፡ ይህም ድርጊት ከአንድ ጊዜ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ ንጉሡ እዚያ ሲሄድ ከጥበቃ ጋር ነበር፡፡
\v 11 የሶርያ ንጉሥም፡- «ከእኛ መካከል ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ግንኙነት ያለው ማን እንደሆነ አትነግሩኝምን?» ሲል ጠየቃቸው፡፡
\s5
\v 12 ከእነርሱም አንዱ «ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ከእኛ መካከል ይህን የሚያደርግ ማንም የለም፤ በመኝታ ክፍልህ እንኳ ሆነህ የምትናገረውን ሁሉ ሳይቀር ለእስራኤል ንጉሥ ምሥጢሩን የሚገልጥለት ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ ነው» ሲል መለሰለት፡፡
\v 13 የሶርያው ንጉሥ፡- «እርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ፈልጉ፤ እኔም ልኬ እማርከዋለሁ» አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ በዶታይን እንደሚኖር ተነገረው፡፡
\s5
\v 14 ስለዚህ ንጉሡ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ብዙ ሠራዊት ወደ ዶታይን ላከ፡፡ እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ፡፡
\v 15 በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ ከቤት ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማዪቱን መክበባቸውን አየ፡፡ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ: - «ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?» ሲል ጠየቀው፡፡
\v 16 ኤልሳዕም «አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል» አለው፡፡
\s5
\v 17 ኤልሳዕም «እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!» ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን አገልጋይ ዐይኖች ከፈተለት፤ በኮረብታው ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ እንዳሉ ተመለከተ፡፡
\v 18 ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ እንዲህ ሲል ጸለየ፡- «እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!» እግዚአብሔርም ኤልሳዕ እንደ ጸለየው፣ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ፡፡
\v 19 ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ሶርያውያንን፡- «መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልምራችሁ፣ ተከተሉኝ» ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው፡፡
\s5
\v 20 ወደ ሰማርያም በደረሱ ጊዜ ኤልሳዕ፡- «እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ክፈት!» ሲል ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ መካከል መሆናቸውን ተረዱ፡፡
\v 21 የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ «ጌታዬ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?» ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው፡፡
\s5
\v 22 ኤልሳዕም «አይሆንም! እንኳን እነዚህን በሰይፍህና በቀስትህ የማረካቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትንና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ» አለው፡፡
\v 23 ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ፡፡
\s5
\v 24 ከዚህ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ በእስራኤል ላይ በማዝመት ጉዳት አደረሰ፤ የሰማርያን ከተማም ከበበ፡፡
\v 25 ስለዚህ በሰማርያ ጽኑ ራብ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የአንድ አህያ ራስ ሰማኒያ መክሊት ብር፣ ሁለት መቶ ግራም የሚያህል የርግብ ኩስ ዋጋ እስከ አምስት መክሊት ብር ይሸጥ ነበር፡፡
\v 26 አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከታማዪቱ የቅጥር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት: - «ንጉሥ ሆይ እባክህ እርዳኝ!» ስትል ጮኸች፡፡
\s5
\v 27 ንጉሡም «እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት ልረዳሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይንስ ከወይን መጭመቂያው ይመጣልን?
\v 28 ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?» ሲል ጠየቃት፡፡ እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፡- «ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‹ዛሬ ያንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን› ስትል አሳብ አቀረበች፡፡
\v 29 ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‹ልጅሽን አምጪና እንብላ› ብዬ ጠየቅኋት፤ እርስዋ ግን ደበቀችው፡፡»
\s5
\v 30 ንጉሡም ይህንን የሴትዮዋን ቃል በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ በውስጡ ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ፡፡
\v 31 ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ «የዛሬይቱ ጀምበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቆረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!» ሲል ተናገረ፡፡
\s5
\v 32 በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ ከሽማግሌዎች ጋር በቤቱ ተቀምጦ ነበር፡፡ ንጉሡም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ፡፡ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን፡- «ይህ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል» አላቸው፡፡
\v 33 ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ «ይህን መከራ ያመጣው እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ ከዚህ በላይ እግዚአብሔርን የምጠብቀው ለምንድን ነው?» አለ፡፡
\s5
\c 7
\p
\v 1 ኤልሳዕም፡- «እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስማ! ነገ በዚህ ጊዜ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር በሰማርያ በር ይሸመታል» አለ፡፡
\v 2 በዚህ ጊዜ የንጉሡ ባለሥልጣን ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፡- እግዚአብሔር የሰማይ መስኮቶችን እንኳ ቢከፍት ይህ ሊሆን ይችላልን? ኤልሳዕም እንዲህ ሲል መለሰለት፡- ይህ ሲፈጸም በዐኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤፤ አንተ ግን ከዚህ ምንም አትበላም፡፡
\s5
\v 3 አራት ለምጻሞች ከሰማርያ ከተማ በር ቆመው ነበር፡፡ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፡- እስክንሞት ለምን እዚህ እንቀመጣለን?
\v 4 ወደ ከተማ እንግባ ካልን በከተማው ራብ ስላለ እንሞታለን፡፡ ነገር ግን እዚህ ከተቀመጠንም መሞታችን ነው፤ ወደ ሶርያውያን ጦር ሰፈር እንሂድ፤ በሕይወት ካቆዩንም በሕይወት እንኖራለን፤ ከገደሉንም መሞት ብቻ ነው፡፡
\s5
\v 5 ስለዚህም ቀኑ ሊመሽ ሲል ወደ ሶርያውያን ጦር ሰፈር ሊሄዱ ተነሡ፤ ወደ ሰፈሩም በደረሱ ጊዜ እዚያ ማንም አልነበረም፡፡
\v 6 ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር የሶርያ ጦር የፈረሶች፣ የሠረገሎችና ሌሎችንም ከፍተኛ የሠራዊት ድምፅ እንዲሰሙ አድርጎ ስለነበረ ነው፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- የእስራኤል ንጉሥ የሒታውያንና የግብፃውያንን ሠራዊት ቀጥሮ እኛን እያጠቃ ነው፡፡
\s5
\v 7 ስለዚህ ሠራዊቱ በሌሊት ተነሥቶ ሸሸ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና በሰፈሩ ያለውን ሁሉ ትተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሹ፡፡
\v 8 ለምጻሞቹም ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ወደ አንዱ ድንኳን በገቡ ጊዜ በሉ፣ ጠጡ፤ ብር፣ ወርቅና ልብስም ወስደው ደበቁ፡፡ እንደገና ተመልሰው ወደ ሌላ ድንኳን ገብተው ያለውን ወስደው እንደበፊቱ አደረጉ፡፡
\s5
\v 9 ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፡- መልካም አላደረግንም፡፡ ዛሬ የምሥራች የሚሆን ታላቅ ነገር አግኝተናል፤ ነገር ግን ዝም ብለናል፡፡ እስኪነጋም ዝም ብንል ቅጣት ይደርስብናል፡፡ አሁን ተነሥተን እንሂድና ለንጉሡ ቤተ ሰብ እንንገር፡፡
\v 10 ስለዚህ ሄደው የከተማውን በር ጠባቂዎች ተጣሩ፤ እንዲህ ብለውም ነገሩአቸው፡- ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ማንም አልነበረም፤ አንዲት ድምፅ እንኳን የለም፤ ነገር ግን ፈረሶችና አህዮች እንደታሰሩ አሉ፣ እንዲሁም ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው፡፡
\v 11 ከዚያም የበር ጠባቂዎቹ ወሬውን ተናገሩ፤ ከዚያም እስከ ንጉሡ ቤተ ሰብ ድረስ ተሰማ፡፡
\s5
\v 12 ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፡- ሶርያውያን የደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደተራብን ስለሚያውቁ ራሳቸውን ለመሰወር ሰፈሩን ለቀው ወደ ገጠር ሄደዋል፤ እንዲህም ይላሉ፡- ምግብ ፍለጋ ከከተማ ሲወጡ በሕይወት እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንወስዳቸዋለን፡፡
\v 13 ከንጉሡም ባለሥልጣናት አንዱ መልሶ እንዲህ አለ፡- ጥቂት ሰዎች ከሞት ከተረፉት አምስት ፈረሶች እንድንወስድ እለምንሃለሁ፡፡ በዚህ ከተማ የተረፈው ሕዝብ ከዚህ በፊት እንደሞቱ ሰዎች ሁሉ ከሞት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሆነውን ነገር ለማወቅ እንድንችል እነርሱን እንላክ፡፡
\s5
\v 14 ንጉሡም ሁለት ሠረገላዎችን ከፈረሶች ጋር ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ እንዲህ ሲል ላካቸው፡- ሂዱና ተመልከቱ፡፡
\v 15 እነርሱም ከሶርያውያን ኋላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ በየመንገዱም ሁሉ ሶርያውያን ሲሸሹ ጥለው የሄዱትን ብዙ ልብስና መሣሪያ ሁሉ አገኙ፡፡ መልእክተኞቹም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት፡፡
\s5
\v 16 ሕዝቡ ሄደው የሶርያውያንን ሰፈር ዘረፉ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ከዚህ በፊት እንደተናገረው ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም አምስት ኪሎ የገብስ ዱቄት በአንድ ብር ተሸመተ፡፡
\v 17 ንጉሡም የከተማዪቱ ቅጥር በር በባለሥልጣኑ ኃላፊነት እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ያንን አገልጋይ ሕዝቡ ረጋጦት በዚያው ሞተ፡፡ ይህም የሆነው ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው ለማነጋገር በሄደ ጊዜ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነበር፡፡
\s5
\v 18 ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሡ፣ በዚህ ጊዜ በሰማርያ ከተማ በር ሦስት ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ብር ይሸመታል ብሎት ነበር፡፡
\v 19 በዚያም ባለሥልጣኑ ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ሲል መልሶ ነበር፡- እግዚአብሔር የሰማይ መስኮቶችን እንኳ ቢከፍት ይህ እንዴት ይሆናል? ኤልሳዕም፡- ይህ ሲሆን በዐይንህ ብቻ ትመለከታለህ፤ ነገር ግን ከዚህ ምንም አትበላም ብሎት ነበር፡፡
\v 20 እንግዲህ ያ የንጉሡ ባለሥልጣን በሰማርያ ከተማ ቅጥር በር ላይ ሕዝብ ረጋግጦት ለመሞት የበቃው ይህ ትንቢት ስለ ተፈጸመበት ነው፡፡
\s5
\c 8
\p
\v 1 ኤልሳዕም ልጅዋን ከሞት ያስነሣላትን፣ በሱነም የነበረችውን ሴት አስቀድሞ እንዲህ ሲል ነግሮአት ነበር፡- እግዚአብሔር እስከ ሰባት ዓመት የሚቆይ ራብ በዚህች ምድር ላይ ልኮአል፤ ከቤተ ሰብሽ ጋር በሕይወት ለመትረፍ ከዚህ ተነሥተሽ ወደ ሌላ ስፍራ ሂጂ፡፡
\v 2 ስለዚህም የኤልሳዕን ምክር ሰምታ ከነቤተ ሰብዋ ወደ ፍልስጥኤም አገር በመሰደድ እስከ ሰባት ዓመት ቆየች፡፡
\s5
\v 3 ሴቲቱም ከሰባቱ የራብ ዓመቶች ፍፃሜ በኋላ ከፍልስጥኤም አገር ተመልሳ መጣች፤ ስለ መኖሪያ ቤትዋና ስለ እርሻ መሬትዋ ለመጠየቅ ወደ ንጉሡ ሄደች፡፡
\v 4 ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ ከግያዝ ጋር፡- «ኤልሳዕ ስላደረጋቸው ታላላቅ ነገሮች ንገረኝ» እያለ ይነጋገር ነበር፡፡
\s5
\v 5 ግያዝም ኤልሳዕ እንዴት የሞተውን ሕፃን እንዳስነሣው ለንጉሡ እየነገረ እያለ ኤልሳዕ ሕፃኑን ከሞተ ያስነሣላት ሴት ንጉሡን ስለ መኖሪያ ቤትዋና ስለ እርሻ መሬቷ ለመጠየቅ መጣች፡፡ ግያዝም እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሴቲዮዋ እነሆ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጅዋም ይሄ ነው!»
\v 6 ንጉሡም ሴቲቱን ስለ ሕፃኑ በጠየቃት ጊዜ በሚገባ አስረዳችው፡፡ ስለዚህ ንጉሡ አንዱን ባለሥልጣን ስለ እርስዋ እንዲህ ሲል አዘዘ፡- የእርስዋ የሆነውን ማናቸውንም ነገርና የእርሻ መሬትዋን ከሰባት ዓመት ጀምሮ አገሩን ከለቀቀችበት እስካሁን ያለውን ሰብል ጭምር እንዲመልስላት አዘዘው፡፡
\s5
\v 7 የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ በታመመ ጊዜ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፡፡ ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው መምጣቱን ሰማ፡፡
\v 8 ንጉሡም አዛሄልን፡- «በእጅህ አንድ ስጦታ ይዘህ ወደ እግዚአብሔር ሰው ሂድና ከዚህ ሕመም እድናለሁን? ብለህ ጠይቅ አለው፡፡
\v 9 ስለዚህ አዛሄል በደማስቆ ከሚገኘው ምርጥ የምድር በረከት ሁሉ በአርባ ግመሎች ጭኖ ወደ ኤልሳዕ ሄደ፡፡ አዛሄልም መጥቶ በኤልሳዕ ፊት ቆመና፡- «ልጅህ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ከሕመሙ ይድን እንደሆነ እንድትነግረው እጠይቅህ ዘንድ ልኮኛል» አለው፡፡
\s5
\v 10 ኤልሳዕም፡- «ቤን ሀዳድን አንተ በርግጥ ትድናለህ ብለህ ንገረው፣ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል፤» አለው፡፡
\v 11 ከዚያም ኤልሳዕ ፊቱን በማጥቆር ትኩር ብሎ እስኪያፍር ድረስ አዛሄልን ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው እንባውን ማፍሰስ ጀመረ፡፡
\v 12 አዛሄልም፡- «ጌታዬ ስለምን ታለቅሳለህ?» ሲል ጠየቀው፡፡ ኤልሳዕም፡- «በእስራኤል ሕዝብ ላይ የምትፈፅመውን አሰቃቂ ነገር ስለማውቅ ነው፡፡ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ወጣቶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናቶቻቸውን በድንጋይ ትከሰክሳለህ፤ የእርጉዞች ሴቶችንም ሆድ ትሰነጥቃለህ» ሲል መለሰለት፡፡
\s5
\v 13 አዛሄልም፡- «ይህን ታላቅ ነገር የሚያደርግ አገልጋይህ ማን ሆኖ ነው? ይህ ሰው ውሻ ብቻ ነው ሲል ጠየቀው፡፡ ኤልሳዕም፡- «አንተ የሶርያ ንጉሥ እንደምትሆን እግዚአብሔር ገልጦልኛል» ሲል መለሰለት፡፡
\v 14 ከዚያም አዛሄል ተመልሶ ወደ ጌታው ወደ ንጉሡ መጣ፡፡ «ኤልሳዕ ምን አለህ?» ሲል ቤን ሀዳድ ጠየቀው፡፡ አዛሄልም፡- «አንተ በእርግጥ እንደምትድን ነግሮኛል» ሲል መለሰለት፡፡
\v 15 ነገር ግን በማግስቱ አዛሄል ብርድ ልብስ ወስዶ ውሃ ውስጥ ነከረ፤ ከዚያም በቤን ሀዳድ ፊት ወረወረውና ታፍኖ ሞተ፡፡ አዛሄልም በቤን ሀዳድ ፈንታ ተተክቶ የሶርያ ንጉሥ ሆነ፡፡
\s5
\v 16 የእስራኤል ንጉሥ የአክአብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት ኢዮራም በይሁዳ መንገሥ ጀመረ፡፡ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ልጅ ነበር፡፡
\v 17 እርሱም በነገሠ ጊዜ ሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነበር፡፡ መቀመጫውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ነገሠ፡፡
\s5
\v 18 ሚስቱም የአክዓብ ልጅ ስለነበረች የእስራኤል ነገሥታት ይፈፅሙት የነበረውን እንደ አክዓብ ቤተ ሰብ የክፋት መንገድ ተከተለ፡፡ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡
\v 19 ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዘሩ መንግሥታትን እንደማያጠፋ ለአገልጋዩ ለዳዊት ተስፋ ሰጥቶት ስለ ነበር ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፡፡
\s5
\v 20 በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐመፀ፤ ለራሳቸውም ንጉሥ አነገሡ፡፡
\v 21 ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን በመላ አሰልፎ ወደ ጸዒር ዘመተ፡፡ የኤዶም ሠራዊትም ኢዮራምን በከበቡ ጊዜ፤ በሌሊት ተነሥተው የሠረገሎቹን አዛዦች አጠቁአቸው፤ ነገር ግን የኢዮራም ሠራዊት ሮጠው ወደየቤታቸው ተበታተኑ፡፡
\s5
\v 22 ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤዶም በይሁዳ አገዛዝ ላይ አመፁ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም የልብና ከተማ አመፀች፡፡
\v 23 ኢዮራም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ የነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
\v 24 ኢዮራም ሞተ፤ በዳዊት ከተማም በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ ከዚያም አካዝያስ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ነገሠ፡፡
\s5
\v 25 የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 26 አካዝያስ በነገሠ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ወጣት ነበረ፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱ ጎቶልያ ተብላ የምትጥራው የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች፡፡
\v 27 አካዝያስ የንጉሥ አክዓብን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፡፡ ምክንያቱም አካዝያስ የንጉሥ አከዓብን ልጅ ስለሚያገባ ነበር፡፡
\s5
\v 28 አካዝያስም ከንጉሥ አከዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር ሆኖ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር ለመዋጋት ወደ ራሞት ገለዓድ ዘመተ፡፡ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቆሰሉት፡፡
\v 29 ኢዮራምም ከሶሪያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በሬማት በተደረገው ጦርነት የደረሰበትን ቁስሉን ለመታከም ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ተመለሰ፡፡ ስለዚህ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የአከዓብ ልጅ ኢዮራም ስለደረሰበት ጉዳት ለመጠየቅ ወደ ኢይዝራኤል ከተማ ሄደ፡፡
\s5
\c 9
\p
\v 1 ነቢዩ ኤልሳዕም ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፡- «በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ሬማት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፡፡
\v 2 እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሳፍጥ ልጅ የናሜሲ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በመለየት ወደ ውስጥ አስገባው፡፡
\v 3 ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበትና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ‹አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ» ብለህ ንገረው አለው፡፡ ከዚያም በሩን ከፍተህ ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ፤ አትዘገይም፡፡»
\s5
\v 4 ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ሬማት ሄደ፡፡
\v 5 እዚያም በደረሰ ጊዜ የጦር አዛዦች ተቀምጠው ነበር፡፡ ወጣቱም ነቢይ እንዲህ አለ፡- «ጌታዬ የምነግርህ መልእክት አለኝ» አለው፡፡ ኢዩም፡ «ለማናችን ነው የምትነግረው?» ሲል ጠየቀው፡፡ ወጣቱም ነቢይ፡- «የምናገረው ለአንተ ነው ጌታዬ» ሲል መለሰለት፡፡
\v 6 ስለዚህ ኢዩ ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ወጣቱ ነቢይም ዘይቱን በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፡- «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፡- ‹በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ፡፡
\s5
\v 7 አንተም የአክዓብን የጌታህን ቤተ ሰብ መግደል አለብህ፤ በዚህም በኤልዛቤል የተገደሉትን፣ የአገልጋዮቼን የነቢያቴንና የእግዚአብሔር አገልጋዮችን ደም በሙሉ እበቀላለሁ፡፡
\v 8 መላው የአክዓብ ቤተ ሰብና ትውልዱ ሁሉ ይጠፋሉ፤ ከእርሱ ቤተ ሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አጠፋለሁ፡፡
\s5
\v 9 የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብአምና በአኪያ ልጅ በባኦስ ቤተሰቦች ላይ ያደርግኹትን ሁሉ በአክዓብ ቤተ ሰብ ላይ እፈፅማለሁ፡፡
\v 10 ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የኤልዛቤልን ሬሳ በኢይዝራኤል ከተማ ውሾች ይበሉታል፤ ማንም አይቀብራትም፡፡» ከዚያም ወጣቱ ነቢይ በሩን ከፍቶ ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ፡፡
\s5
\v 11 ከዚያም ኢዩ ወደ ንጉሡ አገልጋዮች በመጣ ጊዜ አንዱ፡- «ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ወደ አንተ ለምን መጣ?» ሲሉ ጠየቁት፡፡ ኢዩም «ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ» አላቸው፡፡
\v 12 እነርሱም «ይህ ሐሰት ነው፡፡ አንተ ንገረን» ሲሉ መለሱለት፡፡ ኢዩም፡- «በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር ቀብቼሃለሁ»› አለኝ ሲል አስረዳቸው፡፡
\v 13 ከዚያም እነርሱ ወዲያውኑ ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፡፡ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው «ኢዩ ንጉሥ ነው!» ሲሉ ጮኹ፡፡
\s5
\v 14 በዚህ ሁኔታ የኢዮሳፍጥ ልጅ የናሜሲ ልጅ ኢዩ በንጉሥ ኢዮራም ላይ ሤራ ማካሄድ ጀመረ፡፡ ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ አዛሄል ጋር በሬማት ገለዓድና እስራኤል በሙሉ ሲከላከሉ፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ውስጥ በማገገም ላይ ነበር፡፡
\v 15 ስለዚህም ኢዩ የጦር መኮንኖች «እናንተ በእርግጥ ከእኔ ጋር ከሆናችሁ በኢይዝራኤል የሚኖረውን ሕዝብ ለማስጠንቀቅ አንድ ወሬ ከሬማት ወጥቶ እንዳያመልጥ አድርጉ» አላቸው፡፡
\v 16 ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቁስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ነበር፡፡
\s5
\v 17 በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ጠባቂ ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ ከሩቅ አይቶ «ሰዎች እየጋለቡ በቡድን ሲመጡ አያለሁ!» አለ፡፡ ኢዮራምም «አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ» አለው፡፡
\v 18 መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን፡- «ንጉሡ አመጣጥህ በሰላም ነውን?» ይልሃል ሲል ጠየቀው፡፡ ኢዩም፣ «አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!» ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም ጠባቂው፡- «መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም» ሲል ለንጉሡ ነገረው፡፡
\s5
\v 19 ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፡፡ ኢዩም፡- «አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!» ሲል መለሰለት፡፡
\v 20 ጠባቂውም እንደገና፡- «እርሱ ተገናኝቶአል ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም» አለ፡፡ ‹ምክንያቱም የሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ ነው! ልክ ኢዩን ይመስላል!» ሲል ተናገረ፡፡
\s5
\v 21 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፡- «ሠረገላ አዘጋጁልኝ» አለ፡፡ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት ኢዮራም የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላችው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፡፡ እነርሱም ኢዩን የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት፡፡
\v 22 ኢዮራምም፡- «ኢዩ ሆይ አመጣጥህ በሰላም ነውን?» ሲል ጠየቀ፡፡ ኢዩም፡- «የእናትህ የኤልዛቤል የአመንዝራይቱ ጣዖትና ጥንቆላ ሥራ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ?» ሲል መለሰለት፡፡
\s5
\v 23 በመሆኑም ኢዮራም፡- «አካዝያስ ሆይ! ይህ ክሕደት ነው!» እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ፡፡
\v 24 ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኀይል ሁሉ ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል ወደ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ፡፡
\s5
\v 25 ኢዩም ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የጦር አዛዥ «ሬሳውን አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው አለው፡፡ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፡፡
\v 26 ‹ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ› የሚል ነበር፡፡» ስለዚህ ኢዩ «እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈፀም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው» ሲል የጦር አዛዡን አዘዘው፡፡
\s5
\v 27 የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ይህን ባየ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤት ሀጋን ከተማ ሸሸ፡፡ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው «እርሱንም ደግሞ በሠረገላው ውስጥ ግደሉት» አለ፡፡ እነርሱም ተከታትለው በኢዮርብዓም ከተማ አጠገብ በጉር በሠረገላው ሳለ ወጉት፤ አካዝያስም ወደ መጊዶ ከተማ ሸሸ፤ በዚያም ሞተ፡፡
\v 28 አገልጋዮቹም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃብር ቀበሩት፡፡
\s5
\v 29 አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር፡፡
\s5
\v 30 ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል በደረሰ ጊዜ፣ ኤልዛቤል ይህን ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጉርዋንም ተሠርታ በመስኮት ትመለከት ነበር፡፡
\v 31 ኢዩም የቅጥሩን በር አልፎ ሲገባ «አንተ ዘምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ፣ እዚህ ደግሞ የመጣሃው በሰላም ነውን?» አለችው፡፡
\v 32 ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት፡- «ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?» አለ፡፡ ቁጥራቸው ሁለት ወይም ሦስት የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ወደ እርሱ ተመለከቱ፡፡
\s5
\v 33 ኢዩም «ኤልዛቤልን ወደ ታች ወርውሯት!» አላቸው፡፡ እነርሱም አንሥተው በወረወሯት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ ኢዩም ሬሳዋን በፈረስና ሠረገላው ረጋገጠ፡፡
\v 34 ኢዩም ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ተመገበ፤ ጠጣም፡፡ ከዚያም «የንጉሥ ልጅ ነችና ያችን የተረገመች ሴት ቅበሩአት» አለ፡፡
\s5
\v 35 ሊቀብሩዋት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፣ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ መዳፍ በቀር ምንም አላገኙም፡፡
\v 36 ይህንንም ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ «ይህ ሁሉ የተፈፀመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ በቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‹የኤልዛቤልን ሬሳ በኢይዝራኤል ውሾች ይበሉታል፡፡
\v 37 ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርሷነቷን ለየቶ በማወቅ፡- ይህች ኤልዛቤል ናት ሊል አይችልም፡፡»
\s5
\c 10
\p
\v 1 በዚህ ጊዜ የአክዓብ ሰባ ትውልድ በሰማርያ ይገኝ ነበር፡፡ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ አንዳንድ ቅጂ ለከተማዪቱ ገዢዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የአክዓብ ትውልድ ጠባቂዎች ሁሉ ላከ፡፡ ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፡-
\v 2 «እናንተ ለንጉሡ ትውልድ፣ ፈረሶችና ሠረገሎች የጦር መሣሪያዎችና የተመሸጉ ከተሞች በእናንተ በእጃችሁ ለሚገኙ ሁሉ ኃላፊዎች ናችሁ፡፡ እንግዲህ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ፡-
\v 3 ከንጉሡ ትውልድ የተሻለውን አንዱን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አንግሡት፤ ለእርሱም ለሥርወ መንግሥቱ ተዋጉለት!» የሚል ነበር፡፡
\s5
\v 4 ነገር ግን እነርሱም በፍርሃት ተሸብረው «ንጉሥ ኢዮራምና ንጉሥ አካዝያስ ሊቋቋሙት ያልቻሉትን እኛ እንዴት ኢዩን ልንቋቋመው እንችላለን?» አሉ፡፡
\v 5 ስለዚህም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊና የከተማዪቱ ገዢ ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና ከአሳዳጊ ሞግዚቶች ጋር በመተባበር ለኢዩ «እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ አንተ የምታዘንን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ አንተ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ» ሲሉ መልእክት ላኩ፡፡
\s5
\v 6 ኢዩም፡- «እናንተ ከእኔ ጋር ከተባበራችሁና ትእዛዜንም ለመፈፀም ዝግጁዎች ከሆናችሁ ነገ በዚህ ጊዜ የንጉሥ አክዓብን ዘሮች ሁሉ ራሶቻቸውን ቆርጣችሁ ወደ ኢይዝራኤል ይዛችሁልኝ እንድትመ›ጡ› ሲል ሌላ ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ ሰባውም የንጉሥ አክዓብ ትውልድ በታወቁ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ ሥር ነበሩ፡፡
\v 7 የኢዩ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው የሰማርያ መሪዎች ሰባውንም የአክዓብ ተወላጆች በሙሉ ገደሉ፤ ራሶቻቸውንም በመቁረጥ በቅርጫት ሞልተው በኢይዝራኤል ወደ ነበረው ወደ ኢዩ ላኩለት፡፡
\s5
\v 8 ኢዩም የአክዓብ ትውልድ ራሶች ተቆርጠው መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በከተማይቱ ቅጥር በር በሁለት ረድፍ ተከምረው እስከ ተከታዩ ቀን ጠዋት ድረስ እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጠ፡፡
\v 9 በማግስቱ ማለዳ ላይ ኢዩ ወደ ከተማይቱ ቅጥር በር ሄዶ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ «በንጉሥ ኢዮራም ላይ በማሤር የገደልኩት እኔ ነበርኩ፤ ስለዚህም እናንተ በዚያ ጉዳይ አትጠየቁበትም፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የገደለ ማነው?
\s5
\v 10 ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈፅሞታል፡፡»
\v 11 ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶችና ባለሥልጣናት የነበሩትን እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ፡፡
\s5
\v 12 ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም «የእረኞች ሰፈር» ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፡-
\v 13 ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ «እናንተ እነማን ናችሁ?» ሲል ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተ ሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው» ሲሉ መለሱለት፡፡
\v 14 ኢዩም «እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!» ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸው፤ ኢዩም በዚያው በቤት ኤክድ አጠገብ ገደላቸው፡፡ ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም፡፡
\s5
\v 15 ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጉዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ «የእኔ ልብ ከአንተ ጋር እንደ ሆነ የአንተ ልብ ከእኔ ጋር ነውን?» ሲል ጠየቀው፡፡ ኢዮናዳብም «አዎን ከአንተ ጋር ነው» ሲል መለሰለት፡፡ ኢዩም «እንግዲያውስ ጨብጠኝ» ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠው፡፡
\v 16 «ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ታማኝ እንደ ሆንኩ ራስህ ተመልከት» አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ፡፡
\v 17 ወደ ሰማርያ በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር በሰማርያ ያሉትን የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር፡፡
\s5
\v 18 ከዚያም ኢዩ የሰማርያን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ «ንጉሥ አክዓብ ባዓልን ያገለገለው በመጠኑ ነበር፤ እኔ ግን ከእርሱ ይበልጥ ላገለግለው እፈልጋለሁ፤
\v 19 ስለዚህም የባዓልን ነቢያት በሙሉ ባዓልን የሚያመልኩትንና ካህናቱን ጭምር በአንድነት ጠርታችሁ ሰብስቡልኝ፤ በምንም ምክንያት የሚቀር አይኑር፤ እኔ ለባዓል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ በዚያ የማይገኝ ማንም ሰው ቢኖር በሕይወት አይኖርም፡፡» ይህም ሁሉ ባዓልን የሚያመልኩትን ሁሉ ለመግደል ኢዩ ያቀደው የተንኮል ዘዴ ነበር፡፡
\v 20 ከዚህም በኋላ ኢዩ «ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት ክብረ በዓል ይደረግ!» ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህም በዐዋጅ ተነገረ፡፡
\s5
\v 21 ኢዩም በእስራኤል ምድርና ባዓልን ለሚያመልኩ ሁሉ መልእክት ላከ፡፡ ማንም ከጫፍ እስከ ጫፍ ሳይመጣ የቀረ አልነበረም፤ ሁሉም ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ገብተው ዳር እስከ ዳር ሞሉት፡፡
\v 22 ከዚያ ኢዩ የተቀደሱ አልባሳት ኀላፊ የሆነው ካህን አልባሳትን ሁሉ አውጥቶ ለባዓል አምላኪዎች እንዲያመጣላቸው አዘዘ፡፡ እንደታዘዘውም አልባሳቱን አመጣላቸው፡፡
\s5
\v 23 ስለዚህም ኢዩ ራሱ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር አብሮ ወደ ባዓል ቤተ መቅደሱ ገባ፤ በዚያም ለሕዝቡ በዚህ የሚገኙት የባዓል አምላኪዎች ብቻ መሆናቸውንና እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንድም አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ ሲል ተናገረ፡፡
\v 24 ከዚያም እርሱና ኢዮናዳብ ለባዓል ልዩ ልዩ መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ለማቅረብ ሄዱ፡፡ ኢዩም በባዓል ቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰማኒያ ወታደሮች በማሰለፍ እነዚህን ሁሉ ሰዎች እንድትገድሉ፣ ከእነርሱ አንድ እንኳ የሚያመልጥ ሰው ቢኖር በዚያ ሰው ምትክ እርሱ ራሱ ይገደላል ሲል መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር፡፡
\s5
\v 25 ኢዩ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ወዲያውኑ ለጠባቂዎችና ለአዛዡ፡- ሂዱና ማንም ሰው እንዳያመልጥ ግደሉአቸው አለ፡፡ እነርሱም በሰይፍ ስለት ሁሉንም ገደሉአቸው፤ ሬሳቸውንም ሁሉ እየጎተቱ ወደ ውጪ ጣሉ፤ ጠባቂና የጦር አዛዦቹ ወደ ባዓል ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ገቡ፡፡
\v 26 ከዚያም በባዓል ቤተ መቅደስ የነበረውን የድንጋይ ዐምዶች ወደ ውጪ አውጥተው በእሳት አቃጠሉት።
\v 27 ከዚያም የባዓል አምላኪዎቹን አጸድ አፍርሰው የባዓልን ቤተ መቅደስ አጠፉ፤ እስከዛሬ ድረስ ቤተ መቅደሱንም መጸዳጃ እንዲሆን አደረጉት፡፡
\v 28 ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የባዓልን አምልኮ ያስወገደው በዚህ ዓይነት ነበር፡፡
\s5
\v 29 ነገር ግን ኢዩ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን፣ በቤተልና በዳን፣ የወርቅ ጥጃ የጣዖት ማምለኪያ ምስል ያቆመበትን የኃጢአት መንገድ አልተከተልም፡፡
\v 30 ስለዚህም እግዚአብሔር ኢዩን፡- በአክዓብ ትውልድ ሁሉ ላይ ልታደርግ የሚገባህን በዐይኖቼ ፊት ትክክል የሆነውን ፈጽመሃል፤ ከዚህም የተነሣ የአንተ ትውልድ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ላይ እንደሚነግሡ የተስፋ ቃል እስጥሃለሁ አለው፡፡
\v 31 ኢዩ ግን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልተመለሰም፡፡
\s5
\v 32 በዚያም ዘመን እግዚብሔር የእስራኤልን ግዛት እንዲቀነስ አደረገ፤ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤልን ድል ነሥቶ የእስራኤልን ግዛት ድንበሮች ያዘ፡፡
\v 33 እርሱም የያዘው ግዛት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በስተ ደቡብ በኩል ከአርኖን ወንዝ በላይ እስከምትገኘው እስከ አሮዔር ከተማ የሚደርስ ሲሆን ይህም የጋድ የቶቤልና በምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩባቸው የነበሩትን ሸለቆ የገለዓድንና የባሳንን ግዛቶች ያጠቃልላል፡፡
\s5
\v 34 ኢዩ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
\v 35 ከዚህም በኋላ ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ፡፡
\v 36 ኢዩም በሰማርያ እስራኤልን ለሃያ ስምንት ዓመት ገዛ፡፡
\s5
\c 11
\p
\v 1 የንጉሥ አካዝያስ እናት ጎቶልያ የልጅዋን መገደል እንደ ሰማች ተነሥታ የንጉሣውኑን ቤተ ሰብ አባላት በሙሉ ገደለች፡፡
\v 2 ከእርስዋም እጅ ማምለጥ የቻለ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ ነገር ግን አክስቱ የነበረችው በአባትዋ በኩል የንጉሥ አካዝያስ እኅት የንጉሥ ኢዮራም ልጅ ዮሳቤት ከሞቱት ከንጉሥ ልጆች መካከል ወስዳ በመደበቅ ከሞት አዳነችው፤ እርሰዋም ሞግዚቱን ወስዳ በቤትዋ መኝታ ክፍል ውስጥ ስለደበቀችው በጎቶልያ እጅ ሳይገደል ቀረ፡፡
\v 3 ጎቶልያ በነገሠችበት ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዮሳቤት ሕፃኑን ኢዮአስን በመደበቅ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመንከባከብ አሳደገችው፡፡
\s5
\v 4 ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ለንጉሡ ክብር ዘቦችና ለቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ሁሉ ኃላፊ ወደሆኑት የጦር አዛዦች ሁሉ ልኮ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አስጠራቸው፤ በዚያም ሊያደርገው ያቀደውን ይስማሙበት ዘንድ በመሐላ እንዲያረጋግጡለት አደረገ፤ ከዚያም በኋላ የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን አሳያቸው፡፡
\v 5 የሚከተለውንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ በሰንበት ቀን ለጥበቃ በምትሰማሩበት ጊዜ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤
\v 6 ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ የሱርን የቅጥር በር ይጠብቅ፤ የቀረው አንድ ሦስተኛ እጅ ደግሞ ከሌሎቹ ጥበቃዎች በስተኋላ ያለውን ቅጥር በር ይጠብቅ፡፡
\s5
\v 7 በሰንበት ቀን ከጥበቃ ነጻ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ንጉሡን ለመከላከል ቤተ መቅደሱን ይጠብቁ፤
\v 8 ንጉሥ ኢዮአስን በዙሪያው በምትጠብቁበትም ጊዜ ሰይፋችሁን መዛችሁ ወደሚሄድበት ስፍራ ሁሉ አብራችሁ ሂዱ፤ ወደ እናንተ ለመቅረብ የሚደፍር ማንም ቢኖር ይገደል፡፡ ንጉሡ ሲወጣና ሲገባ ከእርሱ አትለዩ፡፡
\s5
\v 9 የጦር አዛዦቹም ካህኑ ዮዳሄ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በሰንበት ቀን ለጥበቃ የሚሰማሩትንና ከጥበቃም የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ጭምር አሰልፈው ወደ ካህኑ ዮዳሄ አመጡ፡፡
\v 10 ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮችና ጋሻዎች አውጥቶ ለጦር አለቆቹ ሰጣቸው፡፡
\s5
\v 11 ጭፍሮቹም ሰይፋቸውን እንደ መዘዙ ንጉሡን ከበው በቤተ መቅደሱ በቀኝና በግራ በመሠዊያው አጠገብ እንዲቆሙ አደረጋቸው፡፡
\v 12 ከዚያም ዮዳሄ ኢዮአስን አቅርቦ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነለት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጂ አስረከበው፤ በዚህ ዓይነት ኢዮአስ ተቀብቶ ነገሠ፡፡ ሕዝቡም በእጃቸው እያጨበጨቡ፣ ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ አሉ፡፡
\s5
\v 13 ንግሥት ጎቶልያ የክብር ዘቦቹንና የሕዝቡን ጩኸት ድምፅ በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መጣች፡፡
\v 14 እዚያ እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባሕል መሠረት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ ቆሞ አየቸው፤ እርሱም በጦር አዛዦችና በእምቢልታ ነፊዎች ታጅቦ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል እያሉ እምቢልታ ይነፉ ነበር፤ ጎቶልያ በድንጋጤ ልብስዋን ቀዳ ይህ በክሕደት የተፈጸመ ሤራ ነው ስትል ጮኸች፡፡
\s5
\v 15 ዮዳሄም የጦር አለቆችን ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል ጎቶልያን አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርስዋን ለመከተል የሚሞክር ቢኖር ይገደል ሲል አዘዛቸው፡፡
\v 16 እነርሱም እርስዋን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያ የፈረስ መግቢያ ቅጥር በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት፡፡
\s5
\v 17 ዮዳሄ፣ ንጉሡና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ከእግዘአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፤ እንዲሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፡፡
\v 18 ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ሄዶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበረ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት፡፡ ዮዳሄም ቤተ መቅደሱን በየተራ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ፤
\s5
\v 19 ከዚህም በኋላ እርሱ፣ የጦር አለቆች፣ የንጉሡ የክብር ዘብና የቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ንጉሡን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት አጅበው እንዲሄዱና ሕዝቡም ሁሉ ከኋላ እንዲከተል አደረገ፤ ኢዮአስም በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ገብቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፡፡
\v 20 ጎቶልያ በቤተ መንግሥት በሰይፍ ስለ ተገደለች ሰው ሁሉ ተደሰተ፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች፡፡
\s5
\v 21 ኢዮአስም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፡፡
\s5
\c 12
\p
\v 1 ኢዩ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም አርባ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሳብያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፡፡
\v 2 ካህኑም ዮዳሄ ይመክረውና ያስተምረው ስለ ነበር፣ ኢዮአስ በዕድሜው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
\v 3 ነገር ግን በየኮረብታዎቹ ላይ የሚገኙት የአሕዛብ ማምለኪያዎች ስላልተደመሰሱ ሕዝቡ በዚያ ዕጣን እያጠኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፡፡
\s5
\v 4 ኢዮአስም ካህናትን ጠርቶ በቤተ መቅደስ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ መባ ሆኖ የሚገባውን ገንዘብ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አዘዘ፤ ይኸውም ቋሚ ከሆነው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር መባ ሆኖ የሚቀርበውንና በበጎ ፈቃድ ሕዝቡ የሚያመጣውን ስጦታ ሁሉ የሚያጠቃልል ነበር፡፡
\v 5 እያንዳንዱ ካህን ከሚያገለግላቸው ሰዎች የሚገኘውን የገንዘብ መባ ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ገንዘቡንም እንዳስፈላጊነቱ ለቤተ መቅደሱ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሉት ነገራቸው፡፡
\s5
\v 6 ነገር ግን ኢዮአስ እስከ ነገሠበት እስከ ሃያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ላይ ምንም ዓይነት እድሳት አላደረጉም፡፡
\v 7 ስለዚህም ኢዮአስ ዮዳሄንና ሌሎቹንም ካህናት ወደ እርሱ ጠርቶ ቤተ መቅደሱን ያላደሳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዛሬ ጀምሮ የምትቀበሉትን ገንዘብ መያዝ የለባችሁም፤ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ይውል ዘንድ ገንዘቡን አስረክቡ አላቸው፡፡
\v 8 ካናቱም በዚህ ተስማምተው ቤተ መቅደሱን በራሳቸው ለማደስ የነበራቸውን ተግባር አቆሙ፡፡
\s5
\v 9 በዚህ ፈንታ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም ወስዶ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ በስተ ቀኝ በሚገኘው መሠዊያ አጠገብ አኖረው፤ የየዕለቱ ተረኞች የነበሩትም ካህናት ለአምልኮ የሚመጡት ሰዎች የሚሰጡትን የገንዘብ መባ እየተቀበሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡት ነበር፡፡
\v 10 ሣጥኑም በሚሞላበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ እየመጡ ገንዘቡን በመቁጠር በከረጢት እያሰሩ ያኖሩት ነበር፡፡
\s5
\v 11 ትክክለኛውን ሒሳብ አጣርተው ከመዘገቡ በኋላ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ ኃላፊዎች ያስረክቡ ነበር፤ እነርሱም ገንዘቡን ተረክበው ለአናጢዎችና ለግንበኞች ይሰጡ ነበር፡፡
\v 12 ለድንጋይ ጠራቢዎች፣ ለማደሻ አገልግሎት የሚውል እንጨትና ድንጋይ ለሚገዙና እንዲሁም ለልዩ ልዩ አስፈላጊ ነገሮች ለሚውል ተግባር ሁሉ ይከፍሉ ነበር፡፡
\s5
\v 13 ነገር ግን ከብር ለሚሠሩ ጎድጓዳ ሳሕኖች የዐመድ ማጠራቀሚያ ጎድጓዳ ወጭት፣፣ እምቢልታ ወይም ደግሞ ከብርና ከወርቅ ለሚሠሩ ንዋያተ ቅዱሳት ከዚያ ገንዘብ ላይ ተነሥቶ የሚከፈል ሒሳብ አልነበረም፡፡
\v 14 ያ ገንዘብ በሙሉ በቤተ መቅደሱ እድሳት ተግባር ላይ ለተሰማሩት ሠራተኞች ብቻ የሚውል ነበር፡፡
\s5
\v 15 ለሥራው ኃላፊነት የተመረጡትም ሰዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ነበሩ ገንዘቡን የሰጡአቸው ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፡፡
\v 16 ስለ በደልና ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚከፈለው ገንዘብ ግን ለካህናቱ ጥቅም የሚውል እንጂ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡
\s5
\v 17 በዚያ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በጌት ከተማ ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ቀጥሎም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ተመለሰ፡፡
\v 18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስም ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ማለትም ኢዮሳፍ፣ ኢዮራምና አካዝያስ ለእግዚአብሔር ለይተው ያኖሩትን መባና የራሱን መባ ጨምሮ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች የነበረውን ወርቅ ሁሉ በመሰብሰብ ገጸ በረከት አድርጎ ለንጉሥ አዛሄል ላከለት፡፡ ሐዛሄልም ይህን ተቀብሎ ሠራዊቱን ከኢየሩሳሌም መለሰ፡፡
\s5
\v 19 ንጉሥ ኢዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?
\v 20 ከዚህ በኋላ የንጉሥ ኢዮአስ ባለሥልጣኖች አንድ ላይ ተነሥተው አድመውበት ወደ ሲላ ሲሄድ በሚሎ ጥቃት አደረሱበት፡፡
\v 21 የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ኢዮአስን ገደሉት፡፡ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ፡፡
\s5
\c 13
\p
\v 1 የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ በይሁዳ በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በሰማርያ ለዐሥራ ሰባት ዓመት ለመግዛት የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 2 እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ ናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ፡፡ ከክፉ ሥራውም ከቶ አልራቀም፡፡
\s5
\v 3 ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተቆጥቶ ለሶርያ ንጉሥ አዛሄል፣ እንዲሁም ለልጁ ለቤን ሀዳድ በተደጋጋሚ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፡፡
\v 4 ከዚህ በኋላ ኢዮአካዝ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ በእስራኤላውያን ላይ የፈጸመባቸው ግፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ተመልክቶ የኢዮአካዝን ጸሎት ሰማ፡፡
\v 5 ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤልን ከሶርያውያን እጅ ነጻ የሚያወጣቸውን መሪ ላከላቸው፤ እነርሱም ከዚያ በፊት በነበረው ዓይነት በሰላም ኖሩ፡፡
\s5
\v 6 ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ኢዮርብዓም እስራኤልን ወደ ኃጢአት ከመራበት ከክፉ ሥራቸው አልተመለሱም፤ እስካሁንም አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል በሰማርያ ማምለክ ቀጠሉ፡፡
\v 7 ንጉሥ ኢዮአካዝ ከኀምሳ ፈረሰኞች፣ ከዐሥር ሰረገሎችና ከዐሥር ሺህ ወታደሮች በቀር ሌላ የተደራጀ የጦር ኃይል አልነበረውም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ሠራዊቱን የሶርያ ንጉሥ በአውድማ እንዳለ እብቅ አድርጎ ስለ ደመሰሰበት ነው፡፡
\s5
\v 8 ንጉሥ ኢዮአካዝ የፈጸመው ሌላው ተግባርና የጀግንነት ሥራው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 9 ኢዮአካዝም ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ዮአስ ነገሠ፡፡
\s5
\v 10 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ በነገሠ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በሰማርያ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ በዚያም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፡፡
\v 11 እርሱም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ ምሳሌነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\s5
\v 12 ዮአስ የፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው ጀግንነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 13 ከዚህ በኋላ ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያም በሚገኘው መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ፡፡
\s5
\v 14 ነቢዩ ኤልሳዕ በብርቱ ደዌ ታሞ ነበር፤ ተኝቶም ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ሊጠይቀው ሄዶ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ «አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ! አንተ እኮ የእስራኤል ሕዝብ ኀይላቸውና ጋሻ መከታቸው ነህ!» እያለ አለቀሰለት፡፡
\v 15 ኤልሳዕም ንጉሡን «አንድ ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ» ሲል አዘዘው፤ ዮአስም እንደታዘዘው አደረገ ኤልሳዕም
\v 16 ለማስፈንጠር ተዘጋጅ» አለው፤ ንጉሡም እንደታዘዘው አደረገ፤ ኤልሳዕም እጆቹን በንጉሡ እጆች ላይ አኖረ፡፡
\s5
\v 17 ኤልሳዕ «የምሥራቁን መስኮት ክፈት» አለ፤ ንጉሡም ከፈተው፤ ኤልሳዕም «ፍላጻውን አስፈንጥር!» አለው፤ ንጉሡም ፍላጻውን እንዳስፈነጠረ ወዲያውኑ ኤልሳዕ፣ «ፍላጻ ነህ፤ በአንተም አማካይነት እግዚአብሔር ሶርያውያንን ድል ያደርጋል፤ ሶርያውያንን ድል እስክትነሣቸው ድረስ በአፌቅ ከተማ ትወጋቸዋለህ፡፡»
\v 18 ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ንጉሡን «ሌሎቹንም ፍላጻዎች አንሥተህ በእነርሱ ምድርን ምታ!» አለው፡፡ ንጉሡም ምድርን ሦስት ጊዜ መትቶ አቆመ፡፡
\v 19 ይህም ኤልሳዕን አስቆጣው፤ ስለዚህም ንጉሡን «አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መተህ ቢሆን ኖሮ በሶርያውያን ላይ ፍጹም ድልን ትቀዳጅ ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ድል ትነሣቸዋለህ» አለው፡፡
\s5
\v 20 ኤልሳዕም ሞተ፤ ተቀበረም፡፡ ከሞአብ የመጡ አደጋ ጣዮች በየዓመቱ የእስራኤልን ምድር ይወጉ ነበር፡፡
\v 21 አንድ ጊዜ የአንድ ሰው ሥርዓተ ቀብር በሚፈጸምበት ሰዓት በእነዚያ አደጋ ጣዮች መካከል አንድ ቡድን ሲመጣ ስለታየ የሚቀበረውን ሬሳ ወደ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ በችኮላ በመወርወር ጥለውት ሸሹ፤ ያም ሬሳ ከኤልሳዕ አስክሬን ጋር በተገናኘበት ቅጽበት ወዲያውኑ ከሞት ተነሥቶ ቆመ፡፡
\s5
\v 22 ኢዮአካዝ በነገሠበት ዘመን ሁሉ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤላውያንን በመውረር ያስጨንቃቸው ነበር፤
\v 23 እግዚአብሔር ግን በቸርነቱ ምሕረትን በማድረግ ረዳቸው እንጂ እንዲደመሰሱ አልፈቀደም፤ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የሰጠውን ቃል ኪዳን በማሰብ ሕዝቡን ስላልረሳው ነው፡፡
\v 24 የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በሞተ ጊዜ፣ በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ልጁ ቤን ሀዳድ ነገሠ፡፡
\v 25 ከዚህም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ቤን ሀዳድን ሦስት ጊዜ ድል ነሥቶ በኢዮአካዝ ዘመነ መንግሥት ቤን ሀዳድ ይዞአቸው የነበሩትን ከተሞች አስመለሰ፡፡
\s5
\c 14
\p
\v 1 የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 2 እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ከኢየሩሳሌም ዮዓዳን ተብላ የምትጠራ ነበረች፡፡
\v 3 አሜስያስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቶአል፤ ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞ አያቱ እንደ ንጉሥ ዳዊት አልነበረም፤ እንደ ዳዊት በመሆን ፈንታ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ፡፡
\s5
\v 4 ይኸውም በየኮረብታዎቹ ላይ የተሠሩትን የአሕዛብ ማምለኪያዎችን አላፈረሰም፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ በየኮረብታዎቹ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጠኑን እንደቀጠለ ነበር፡፡
\v 5 አሜስያሰ መንግሥቱን አደላድሎ እንደ ያዘ ወዲያውኑ፣ ቀደም ሲል ነግሦ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ባለሥልጣኖች በሞት ቀጣ፤
\s5
\v 6 ይሁን እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም፤ ይልቁንም በኦሪት ሕግ እግዚአብሔር «ልጆቻቸው በፈጸሙት ኃጢአት ወላጆች በሞት አይቀጡበትም፤ ወላጆችም በፈጸሙት ኃጢአት ልጆች በሞት አይቀጡበትም፤ እያንዳንዱ ሰው ራሱ በፈጸመው ወንጀል ብቻ በሞት ይቀጣል» ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ፈጽሞአል፡፡
\v 7 አሜስያስ «የጨው ሸለቆ» እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ዐሥር ሺህ የሚሆኑ የኤዶም ወታደሮችን ፈጀ፤ ሴላ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ይዞ «ዮቅትኤል» ብሎ ጠራት፤ እስከ አሁንም በዚሁ ስም ትጠራለች፡፡
\s5
\v 8 ከዚህ በኋላ አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን በመላክ «እንግዲህ ና ፊት ለፊት ጦርነት እንግጠም!» ሲል ለጦርነት አነሣሣው፡፡
\v 9 ንጉሥ ዮአስ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት «አንድ ጊዜ በሊባኖስ ተራራ ላይ የምትገኝ ኩርንችት የሊባኖስ ዛፍ ‹ለወንድ ልጄ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሴት ልጅህን ስጠኝ› ስትል መልእክት ላከችበት፤ ነገር ግን አንድ የሊባኖስ አውሬ እግረ መንገዱን በዚያ ሲያልፍ ስለ ረገጣት ያቺ ኩርንችት ሞተች፡፡
\v 10 አሜስያስ ሆይ! እነሆ አንተ ኤዶማውያንን ድል ስላደረግህ ልብህ በትዕቢት ተሞልቶአል፤ ባገኘኸውም ድል በመደሰት ዐርፈህ በቤትህ ብትቀመጥ ይሻልሃል፤ በአንተና በሕዝብህ ላይ መከራና ውድቀት ስለ ምን ታስከትላለህ?»
\s5
\v 11 አሜስያስ ግን የዮአስን መልስ ከምንም አልቆጠረውም፤ ስለዚህም ንጉሥ ዮአስ ሠራዊቱን አስከትሎ በአሜስያስ ላይ በመዝመት በይሁዳ ምድር በምትገኘው በቤት ሳሚስ ጦርነት ገጠመው፡፡
\v 12 ይሁዳም ድል ተመታ፤ ወታደሮቹም ሁሉ ተበታትነው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
\s5
\v 13 ዮአስም የአካዝያስን ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመድረስ ገሠገሠ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ከኤፍሬም ቅጥር በር «የማዕዘን ቅጥር በር» ተብሎ እስከሚጠራው በር ድረስ ጠቅላላ ርዝመቱ ሁለት መቶ ሜትር የሆነውን የቅጥር ግንብ አፈረሰ፡፡
\v 14 በዚያም ያገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ፣ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅዱሳትና የቤተ መንግሥቱን ሀብት ሁሉ ጭኖ ወደ ሰማርያ ተመለሰ፤ በመያዣ ስም የተማረኩ ሰዎችንም ይዞ ሄደ፡፡
\s5
\v 15 ንጉሥ ዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ባደረገው ጦርነት የፈጸመው የጀግንነት ሥራ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 16 ዮአስ ሞተ፤ በሰማርያ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነገሠ፡፡
\s5
\v 17 የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የዮአስ ልጅ አሜስያስ ዐሥራ አምስት ዓመት ቆየ፡፡
\v 18 አሜስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 19 አሜስያስን ለመግደል በኢየሩሳሌም ሤራ ተጠንስሶ ነበር፤ ስለዚህ አሜስያስ ሸሽቶ ወደ ለኪሶ ከተማ ሄደ፤ ነገር ግን ጠላቶቹ ወደ ለኪሶ ሰዎችን ልከው እዚያ አስገደሉት፡፡
\s5
\v 20 ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡
\v 21 የይሁዳም ሕዝብ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጁ የነበረውን ዓዛርያስን አነገሡት፤
\v 22 ዓዛርያስም ቀድሞ ተይዛ የነበረችውን ኤላትን ከአባቱ ሞት በኋላ በጦር ኃይል ድል ነሥቶ አስመልሶ እንደገና ሠራት፡፡
\s5
\v 23 የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ አርባ አንድ ዓመት ገዛ፡፡
\v 24 ዳግማዊ ኢዮርብዓምም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ ከእርሱ በፊት የነበረውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\v 25 ቀድሞ የእስራኤል ይዞታ የነበረውን በስተሰሜን ከሐማት መተላለፊያ ጀምሮ በስተ ደቡብ እስከ ሙት ባሕር የሚገኘውን ግዛት ሁሉ ድል ነሥቶ እንደገና አስመለሰ፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው በጋትሔፌር ተወላጅ አገልጋይ በሆነው በአሚታይ ልጅ በነቢዩ ዮናስ አማካይነት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ነበር፡፡
\s5
\v 26 እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን አሠቃቂ መከራ ተመለከተ፤ በእስራኤል ውስጥ ባርያዎችም ሆኑ ነጻ ሰዎች ረዳት አልነበራቸውም፡፡
\v 27 ይሁን እንጂ እነርሱ ለዘለዓለም ፈጽሞ እንዲደመሰሱ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፤ ስዚህ በዳግማዊ ኢዮርብዓም አማካይት አዳናቸው።
\s5
\v 28 ዳግማዊ ኢዮርብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፣ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነት፣ እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩት ደማስቆና ሐማት ለእስራኤል እንዲመለሱ ያደረገበት ታሪካዊ ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 29 ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ሞተ፤ በነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ዘካርያስ ነገሠ፡፡
\s5
\c 15
\p
\v 1 ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 2 እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበረ፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች፡፡
\v 3 እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
\s5
\v 4 ነገር ግን በየኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋቸውም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኮረብቶቹ ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤
\v 5 በኋላም እግዚአብሔር ዓዛርያስን በቆዳ በሽታ መታው፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቆየው ልጁ ኢዮአታም ነበር፡፡
\s5
\v 6 ንጉሥ ዓዛርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 7 ዓዛርያስም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ፡፡
\s5
\v 8 ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ስድስት ወር ገዛ፡፡
\v 9 እርሱም ከእርሱ በፊት እንደ ነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት መራ፤ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፡፡
\s5
\v 10 ሰሎም ተብሎ የሚጠራው የኢያቤስ ልጅ ሤራ በማድረግ ይብልዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ ፈንታ ነገሠ፡፡
\v 11 ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 12 በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ ሲል የተናገው የተስፋ ቃል ተፈጸመ፡፡
\s5
\v 13 ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በሰማርያ አንድ ወር ብቻ ገዛ፡፡
\v 14 ምናሔ ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን ገድሎም በእርሱ ፈንታ ነገሠ፡፡
\s5
\v 15 ሰሎም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 16 ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ የቲፍሳን ከተማ ነዋሪዎችና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፡፡ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ፡፡
\s5
\v 17 ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፡፡ እርሱም በሰማርያ ዐሥር ዓመት ገዛ፡፡
\v 18 እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የኢርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\s5
\v 19 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ፎሐ እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለፎሐሰጠው፡፡
\v 20 ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እየንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር፡፡ በዚህም ዓይነት ፎሐ በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ፡፡
\s5
\v 21 ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 22 ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ፋቂስያስ ነገሠ፡፡
\s5
\v 23 ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ሁለት ዓመት ገዛ፡፡
\v 24 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\s5
\v 25 በፋቂስያስ ሠራዊት መካከል ፋቁሔ ተብሎ የሚጠራው የሮሜልዩ ልጅ የሆነ አንድ የጦር አዛዥ ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፋቂስያስን ከአርጎብና ከአርዬ ጋር ገድሎ በፋቂስያስ ፈንታ ተተክቶ ነገሠ፡፡
\v 26 ፋቂስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\s5
\v 27 ዓዛርያስ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ነገሠ፤ እርሱም በሰማርያ ሃያ ዓመት ገዛ፡፡
\v 28 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\s5
\v 29 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቴልጌልቴልፌልሶር ዒዮን፣ አቤልቤትመዓካ፣ ያኖዋ፣ ቃዴስና ሐጾር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች እንዲሁም የገለዓድን፣ የገሊላንና የንፍታሌምን ግዛቶች በመውረር ሕዝቡን ወደ አሦር ማርኮ የወሰደው ይኸው ፋቁሔ በነገሠበት ዘመን ነበር፡፡
\v 30 የዖዝያንም ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠ በሃያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በንጉሥ ፋቁሔ ላይ ሤራ ጠነሰሰ፤ እርሱንም ገድሎ በእስራኤል ላይ ነገሠ፡፡
\v 31 ፋቁሔ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\s5
\v 32 የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 33 በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ስድሰት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ኢየሩሳ ተብላ የምትጠራ የሳዶቅ ልጅ ነበረች፡፡
\s5
\v 34 የአባቱንም የዖዝያንን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
\v 35 ነገር ግን በየኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን የአሕዛብን መሠዊያዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጥር በር ያሠራው ይኸው ኢዮአታም ነበር፡፡
\v 36 ኢዮአታም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 37 እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በይሁዳ ላይ አደጋ እንዲጥሉባት የላካቸው ይኸው ኢዮአታም በይሁዳ በነገሠበት ዘመን ነበር፡፡
\v 38 ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብርም ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አካዝ ነገሠ፡፡
\s5
\c 16
\p
\v 1 የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 2 አካዝም በሚነግሠበት ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፡፡ እርሱም የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት አልተከተለም፡፡ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ደስ የማያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
\s5
\v 3 ይልቁንም የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፡፡ የራሱን ልጅ እንኳ ሳይቀር ለጣዖታት የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ይህንንም ድርጊት የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት እግዚአብሔር ከእስራኤል ምድር ያስወገዳቸውን አሕዛብ ይሠሩት የነበረውን አስጸያፊ ድርጊት በመከተል ነበር፡፡
\v 4 አካዝ በየኮረብቶቹ ላይ በተሠሩት የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና በእያንዳንዱም ዛፍ ሥር መሥዋዕት በማቅረብ ዕጣን አጠነ፡፡
\s5
\v 5 የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል መጡ፤ ከበቧትም፡፡ ነገር ግን አካዝን ድል ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡
\v 6 በዚያን ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የኤላትን ከተማ አስመልሶ በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ በዚያ የነበሩትን አይሁድ አስወጣ፡፡ ከዚያም በኤላት የሰፈሩት ኤዶማውያን እስከ አሁንም በዚያ ይኖራሉ፡፡
\s5
\v 7 ስለዚህም ንጉሥ አካዝ ወደ አሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር «እኔ ለአንተ ታማኝ አገልጋይህ ነኝ፤ አደጋ ከጣሉብኝ ከሶርያና ከእስራኤል ነገሥታት እጅ መጥተህ እኔን አድነኝ» በማለት መልእክተኞችን ላከ፡፡
\v 8 አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት የተገኘውን ብርና ወርቅ ሰብስቦ ለዚሁ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት በማድረግ ላከለት፡፡
\v 9 ከዚያም የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር የአካዝን ጥያቄ በመቀበል ዘምቶ ደማስቆን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፡፡ ንጉሥ ረአሶንንም ገደለ፤ ሕዝቡንም ማርኮ ቂር ተብላ ወደምትጠራው ስፍራ ወሰደው፡፡
\s5
\v 10 ንጉሥ አካዝም ከንጉሠ ነገሥት ቴልጌልቴልፌልሶር ጋር ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ፡፡ በደማስቆም አንድ መሠዊያ አየ፡፡ ያንንም መሠዊያ በተመሳሳይ ሁኔታ መሥራት የሚያስችለውን ቅርጽ አዘጋጅቶ ለካህኑ ለኦሪያ ላከለት፡፡
\v 11 ስለዚህ ኦሪያ ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ንድፍ መሠረት መሠዊያ ሠራ፡፡
\v 12 ንጉሡም ከደማስቆ በተመለሰ ጊዜ መሠዊያውን ተመለከተ፤ ወደ መሠዊያው ቀርቦም መሥዋዕት አቀረበ፡፡
\s5
\v 13 በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል የእንስሶች መሥዋዕትና የእህል መባ አቀረበ፡፡ የመባውን ወይን ጠጅና የኅብረት መሥዋዕት ደም አፈሰሰበት፡፡
\v 14 ከነሐስ ተሠርቶ ለእግዚአብሔር የተለየውም መሠዊያ በዚያ አዲስ መሠዊያ፣ በቤተ መቅደሱ መካከል ነበር፤ ያንንም መሠዊያ አስነሥቶ እርሱ ባሠራው በአዲሱ መሠዊያ በስተሰሜን በኩል አኖረው፡፡
\s5
\v 15 ከዚያም ካህኑን ኦሪያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ይህንን የእኔን ታላቅ መሠዊያ ማለዳ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በምሽት ለሚቀርበውም የእህል መባ ስለ ንጉሡና ስለ ሕዝቡ የሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል መባ የሚቀርብበትና የሕዝቡ የወይን ጠጅ መባ የሚፈስበት እንዲሆን አድርግ፤ የሚሠዉትንም የእንስሳት ደም ሁሉ በእርሱ ላይ አፍስስ፤ ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ግን እኔ ራሴ የምፈልገውን ነገር የምጠይቅበት እንዲሆን አድርግ፡፡
\v 16 ካህኑም ኦሪያን ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው አደረገ፡፡
\s5
\v 17 ንጉሥ አካዝም በቤተ መቅደስ ውስጥ መገልገያ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ መንኩራኩሮች ቆርጦ ልሙጥ የሆነውን ነገር ከጎናቸው ወስደ፡፡ በእነርሱ ላይ የነበሩትንም የመታጠቢያ ሳሕኖች ወሰደ፤ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ከታች በኩል ተሸክመውት ከነበሩት ከነሐስ ከተሠሩት ከዐሥራ ሁለት የበሬ ቅርጾች ጀርባ ላይ አንሥቶ ከድንጋይ በተሠራ መሠረት ላይ አኖረው፡፡
\v 18 አካዝ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት የተነሣ በቤተ መቅደሱ የሠሩትን የሰንበት መግቢያ መንገድ ንጉሡ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በውጪው በኩል ከሚገባበት መግቢያ ጋር አስወገደው፡፡
\s5
\v 19 ንጉሥ አካዝ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 20 አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በአባቶቹ መካነ መቃበር ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ፡፡
\s5
\c 17
\p
\v 1 አካዝ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በሰማርያ ዘጠኝ ዓመት እስራኤልን ገዛ፡፡
\v 2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፡፡ ሆኖም እርሱ ያደረገው ኃጢአት ከእርሱ በፊት የነበሩ የእስራኤል ነገሥታት የፈጸሙት አልነበረም፡፡
\v 3 የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ጦርነት በገጠመው ጊዜ ተሸንፎ ሆሴዕ እጁን በመስጠት በየዓመቱ ይገብርለት ጀመር፡፡
\s5
\v 4 ነገር ግን ከጥቂት ዓመቶች በኋላ ንጉሥ ሆሴዕ ሴጎር ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ግብጽ ንጉሥ መልእክተኞች በመላክ ይረዳው ዘንድ ጠየቀው፤ በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ይሰጠው የነበረውንም ግብር አቆመ፡፡ ስልምናሶር ይህን በሰማ ጊዜ ሆሴዕን አስይዞ ወህኒ ቤት አስገባው፡፡
\v 5 ከዚህ በኋላ ስልምናሶር አገሪቱን ወርሮ ሰማርያን ለሦስት ዓመት ከበባት፡፡
\v 6 ከዚያም ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ስልምናሶር ድል አድርጎ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም ማርኮ ወደ አሦር ወሰዳቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን በአላሔ ከተማ፣ ጥቂቶቹን በጎዛን አውራጃ ውስጥ በሚገኘው በአቦር ወንዝ አጠገብ፣ እንዲሁም ሌሎቹን በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡
\s5
\v 7 ይህም ምርኮ የሆነው እስራኤላውያን በሠሩት ኃጢአት ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ በመታደግ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ኃጢአት በመሥራት በማሳዘናቸው ነበር፡፡ ሕዝቡም ባዕዳን አማልክትን አመለኩ፡፡
\v 8 ሕዝቡም ከፊታቸው ያጠፋላቸውን የአሕዛብን መጥፎ ልማድ ተከተሉ፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ያሠራጩትን መጥፎ ልማድ ተቀባዮች ሆኑ፡፡
\s5
\v 9 እስራኤላውያንም አምላካቸው እግዚአብሔር የሚጠላውን ነገር ሁሉ አደረጉ፡፡ ከዘብ ጠባቂዎች ማማ አንሥቶ እስከ ትልቅ ከተማ ድረስ በገጠር ከተሞቻቸው ሁሉ በየኮረብታዎቹ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፡፡
\v 10 በኮረብቶች ሁሉ ላይና በየዛፉ ጥላ ሥር የድንጋይ አምዶችንና አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስሎች አቆሙ፡፡
\s5
\v 11 እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያስወጣቸውን የአረማውያን ሕዝብ ልማድ በመከተል በአሕዛብ መሠዊያዎች ሁሉ ላይ ዕጣን አጠኑ፤ በዚህም ክፉ ሥራቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፤
\v 12 እግዚአብሔርም እንዳያደርጉ የተናገራቸውን ጣዖታትን አመለኩ፡፡
\s5
\v 13 እግዚአብሔርም እስራኤልንና ይሁዳን የሚያስጠነቅቁ መልእክተኞችንና ነቢያትን በመላክ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፤ አገልጋዮቼ በሆኑት ነቢያትና ባለ ራዕዮች አማካይነት ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተም በሰጠሁት ሕጎችና ትእዛዞች የተጻፈውን ሥርዓቱን ጠብቁ ብሎ ነግሮአቸው ነበር፡፡
\s5
\v 14 እነርሱ ግን መታዘዝ አልፈለጉም፤ በአምላካቸው በእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው እልከኞች ሆኑ፡፡
\v 15 የሰጣቸውንም ድንጋጌ አልተቀበሉም፤ ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባውንም ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ የሰጣቸውንም ማስጠንቀቂያዎች ሁሉ ቸል አሉ፤ ለከንቱ ጣዖቶች በመስገድ ራሳቸውም ከንቱዎች ሆኑ፤ የእነርሱን መጥፎ ምሰሌነት እንዳይወርሱ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ ባለመስማት በዙሪያቸው የሚኖሩትን የአሕዛብ ልማድ ሁሉ ተከተሉ፡፡
\s5
\v 16 የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ቸል አሉ፡፡ የሚሰግዱላቸውን ከብረት የተሠሩ ሁለት ጥጆችን አቆሙ፡፡ እንዲሁም አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ሠሩ፣ ለከዋክብትም ሰገዱ፣ ባዓል ተብሎ ለሚጠራውም ባዕድ አምላክ አገልጋዮች ሆኑ፡፡
\v 17 ለእነዚያም አሕዛብ አማልክት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፤ ከሙታን ጠሪዎችና ከጠንቋዮችም ምክር ጠየቁ፤ እግዚአብሔር ለሚጠላው ክፉ ነገር ሁሉ ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሡ፡፡
\v 18 ስለዚሀም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ተቆጥቶ የይሁዳን መንግሥት ብቻ በማስቀረት እስራኤላውያንን ከፊቱ አስወገደ፡፡
\s5
\v 19 የይሁዳ ሰዎችም ቢሆኑ አምላካቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዞች አልጠበቁም ነበር፡፡ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ የተቀበሉትን ልማድ ተከታዮች ነበሩ፡፡
\v 20 ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ሁሉ ተዋቸው፤ ከፊቱም እስኪወገዱ ድረስ ለጠላቶቻቸው አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው፡፡
\s5
\v 21 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከይሁዳ ከለየ በኋላ እስራኤላውያን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መርጠው አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን እንዲተዉ በማድረግ አሠቃቂ ወደ ሆነ ኃጢአት መራቸው፡፡
\v 22 በአገልጋዮቹ ነቢያት ሁሉ አማካይነት እግዚአብሔር እስራኤልን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ እስራኤላውያን የኢዮርብዓምን ኃጢአት ሲሠሩ ኖሩ እንጂ ከዚያ አልራቁም፡፡
\v 23 ስለዚህ እስራኤላውያን ከአገራቸው ተማርከው በመወሰድ እስከ ዛሬ ድስ በአሦር ይኖራሉ፡፡
\s5
\v 24 የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን ኩታ፣ ዓዋና፣ ሐማትና ሴፈርዋይ ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ፡፡
\v 25 እነርሱም በዚያ ሰፍረው መኖር እንደ ጀመሩ እግዚአብሔርን አላመለኩትም ነበር፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አንበሶችን በመላክ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ሰባብረው እንዲገድሉ አደረገ፡፡
\v 26 ለአሦርም ንጉሠ ነገሥት በሰማርያ ከተሞች ሰፍረው እንዲኖሩ ያደረግሃቸው ሕዝቦች የዚያችን አገር አምላክ ሕግ የሚያውቁ ሆነው አልተገኙም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰባብረው የሚገድሉ አንበሶችን ላከባቸው የሚል ወሬ ደረሰው፡፡
\s5
\v 27 ስለዚህ ንጉሠ ነገሥቱ ማርኮ ካመጣቸው ካህናት አንዱን ወደዚያ ላኩ፤ ወደዚያ ተመልሶ በመሄድ የዚያች አገር አምላክ ያዘዘውን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምራቸው አድርጉ ሲል አዘዘ፡፡
\v 28 ስለዚህም ከሰማርያ ተማርኮ የተወሰደ አንድ እስራኤላዊ ካህን ተመልሶ በመሄድ በቤተል ተቀመጠ፤ በዚያ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባቸው አስተማራቸው፡፡
\s5
\v 29 በሰማርያ የሰፈሩት ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን ጣዖት መሥራት ቀጥለው እስራኤላውያን ባሠሩአቸው በከፍተኛ ማምለኪያ ቦታዎች አኖሩአቸው፤ እያንዳንዱ ቡድን በሚኖርበት ከተማ ሁሉ የየራሱን ጣዖት አቆመ፡፡
\v 30 በዚህም ዓይነት የባቢሎን ሰዎች ሱኮትበኖት በተባለው አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ እንዲሁም የኩታ ሰዎች ኤርጌል ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤ የሐማት ሕዝብ አሲማት ተብሎ በሚጠራው ባዕድ አምላክ ስም ጣዖት ሠሩ፤
\v 31 የዓዋ ሕዝብ ኤልባዝርና ተርታቅ ተብለው በሚጠሩ አማልክቶቻቸው ስም ጣዖቶቻቸውን ሠሩ፤ የሴፈርዋይምም ሕዝብ አድራሜሌክና ዓናሜሌክ ተብለው ለሚጠሩ አማልክቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ፡፡
\s5
\v 32 እነዚሁ ሰዎች በተጨማሪ ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ነበር፡፡ ከእያንዳዳቸውም ቡድን በአረማውያን የማምለኪያ ስፍራዎች የሚያገለግሉና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸውን ካህናት መረጡ፡፡
\v 33 በዚህ ዓይነት እግዚአብሔርን ማክበርና ማምለክ ጀመሩ፡፡ በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ይኖሩባቸው በነበሩት ሕዝቦች ይፈጽሙት በነበረው ልማድ መሠረት ለባዕዳን አማልክት ይሰግዱ ነበር፡፡
\s5
\v 34 ይህንኑ አሮጌ ልማዳቸውን እስከ አሁን ድረስ በመፈጸም ላይ ናቸው፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን አያመልኩም ወይም ስሙ እስራኤል ተብሎ ለተጠራው ለያዕቆብ ልጆች እግዚአብሔር በሰጣቸው ደንቦች፣ ሥርዓቶች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ጸንተው አልኖሩም፡፡
\v 35 እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አዞአቸው ነበር፡- ባዕዳን አማልክትን አታምልኩ፣ ለእነርሱም አገልጋዮች በመሆን አትስገዱላቸው፣ መሥዋዕትንም አታቅርቡላቸው፡፡
\s5
\v 36 በታላቅ ኃይልና በሥልጣን ከግብጽ ምድር ላወጣኋችሁ ለእኔ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ መስገድና መሥዋዕት ማቅረብ የሚገባችሁ ለእኔ ብቻ ነው፡፡
\v 37 ጽፌ የሰጠኋችሁንም ድንጋጌና ሥርዓቱን ሕጎችና ትእዛዞቹን ሁልጊዜ ጠብቁ፣ ባዕዳን አማልክትንም አትከተሉ፡፡
\v 38 እኔ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ባዕዳን አማልክትንም አታምልኩ፡፡
\s5
\v 39 እኔን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እኔም ከኃይለኛው ጠላቶቻችሁ እጅ አድናችኋለሁ፡፡
\v 40 ነገር ግን እነዚያ ሕዝቦች ይህን መስማት ትተው አሮጌ ልማዳቸውን ተከተሉ፡፡
\v 41 እነዚያ ሕዝቦች በዚሁ ዓይነት እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ፤ በሌላ በኩል ግን ለጣዖቶቻቸው ይሰግዱ ነበር፤ ዘሮቻቸውም እስከ ዛሬ ድረስ ይህንኑ ዓይነት አምልኮ እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡
\s5
\c 18
\p
\v 1 የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡
\v 2 ሕዝቅያስም ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፡፡ እርሱም በኢያሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም አቢያ የምትባል የዘካርያስ ልጅ ነበረች፡፡
\v 3 ሕዝቅያስም የአባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡
\s5
\v 4 የአሕዛብን የማምለክያ ስፍራዎች አስወገደ፤ የድንጋይ ዐምዶችንም ሰባብሮ አጠፋ፤ ኣሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አፈረሰ፡፡ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ ምክንያቱም እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር፡፡
\v 5 ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፡፡
\s5
\v 6 ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእግዚአብሔር መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር፡፡
\v 7 ስለዚህም እግዚአብሔር ከሕዝቅያስ ጋር ስለነበረ የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ፡፡
\v 8 ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ እስከ ታላቅ የተመሸጉ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት፣ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ አጠቃ፡፡
\s5
\v 9 ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፡፡
\v 10 በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ሆሴዕም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር፡፡
\s5
\v 11 የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን በአላሔ ከተማ፣ ጥቂቶቹን በጋዛ አውረጃ በሚገኘው በአቦር ወንዝ አጠገብ፣ ሌሎቹን ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡
\v 12 ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነበር፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ለመስማትም ሆነ ሕጉን ለመጠበቅ አሻፈረን አሉ፡፡
\s5
\v 13 ከዚያም ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ያዘ፡፡
\v 14 ስለዚህም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም፣ እኔ በድያለሁ፤ እባክህን እኔን ተወኝ፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እልክልሃለሁ ሲል መልእክት ላከ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ለይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እኔ የምፈልገው ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንድትልክልኝ ነው ሲል መለሰለት፡፡
\v 15 ስለዚህም ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥተ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፡፡
\s5
\v 16 እንዲሁም በእግዚዚብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ፡፡
\v 17 ነገር ግን የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከለኪሶ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ሠራዊቱም ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፡፡ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፡፡
\v 18 ከዚያ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም አገልጋዮቹ የሆኑ ሦስት ባለሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፡፡ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነው የኬልቂያስ ልጅ ኤልያቄም፣ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሳምናስና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ነበሩ።
\s5
\v 19 ስለዚህም የአሦር ዋና የጦር አዛዥ እንዲህ አላቸው፡- ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፣ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፡- እንደዚህ የተማመንክበት ነገር ምንድን ነው?
\v 20 በጦርነት የሚረዳ ኃይል እንዳለህ የተናገርከው ከንቱ ቃላት ናቸው፤ በእኔ ላይ ለማመጽ የቻልከው በምን ተማምነህ ነው?
\v 21 የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኮዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲህ ነው’ ሲል ተናገረ፡፡
\s5
\v 22 የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፡- አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ ታስብ እንደሆነ፣ ይህ እንዳይሆን አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው ብለህ ወስነሃል፡፡
\v 23 አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ አንደ ሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ፡፡
\s5
\v 24 አንተ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኮንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
\v 25 እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል፡፡
\s5
\v 26 ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ ይህን የጦር አዛዥ ትርጉሙን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጥር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን አሉት፡፡
\v 27 የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣቸሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት ለሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆነ እኔ የምናገረውን በቅጥር ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት እንድናገር አልላከኝምን? ሲል መለሰላቸው፡፡
\s5
\v 28 ከዚያም የአሦር የጦር አዛዥ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ ጮኸ፡- የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ፤
\v 29 በሕዝቅያስ አትታለሉ፤ እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፡፡
\v 30 ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙት፡፡
\s5
\v 31 ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፡፡
\v 32 ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት። ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፡፡ ስለዚህ ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ይታደጋችኋል” እያለ በመስበክ አያሙኛችሁ፡፡
\s5
\v 33 ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን?
\v 34 ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይ፣ የሄናና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን?
\v 35 የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ንጉሠ ነገሥቶቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?
\s5
\v 36 ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፡፡
\v 37 ከዚያም ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን የጦር አዛዥ የተናገረውን አስረዱት፡፡
\s5
\c 19
\p
\v 1 ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡
\v 2 ወዲያውም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነውን ኤልያቄምን፣ የቤተ መንግሥቱን ጸሐፊ ሳምናስንና ሽማግሌዎች ካህናትን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላከ፤ እነርሱም ራሳቸው ማቅ ለብሰው ነበር፡፡
\s5
\v 3 ለኢሳይያስም እንዲነግሩት የላከው መልእክት ከዚህ የሚከተለው ነው፡- ዛሬ የታላቅ መከራ ቀን ነው፤ የሚያሳፍር ቅጣትና ውርደት እየደረሰብን ነው፤ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ለማማጥ አቅም እንዳነሣት ሴት ሆነናል፡፡
\v 4 የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሕያው እግዚአብሔርን እንዲሰድብለት ከፍተኛ ባሥልጣኑን ልኮአል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ስድብ ሰምቶ ተሳዳቢው ይቀጣ ይሆናል። ስለዚህ ከሕዝባችን መካከል በሕይወት ለተረፉት ሰዎች እባክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡
\s5
\v 5 የንጉሥ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣
\v 6 ኢሳይያስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብላችሁ ለንጉሣችሁ ንገሩት አላቸው፣ የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች ሲሰድቡኝ ስለ ሰማችሁት ቃል አትፍሩአቸው፡፡
\v 7 እነሆ እኔ የሽብር ወሬ የሚያሰማ መንፈስ እልክበታለሁ፤ ስለዚህ ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲሄድ፣ እዚያ በገዛ ምድሩ በሰይፍ ተመትቶ እንዲሞት አደርጋለሁ፡፡
\s5
\v 8 ከዚያ የአሦር የጦር አዛዥ፣ የአሦር ንጉሥ ከሰፈሩ ከለኪሶ ተነሥቶ ልብናን ሊያጠቃ እንደ ሄደ በመስማቱ እርሱም ወደ ለኪሶ ሄደ፡፡
\v 9 በኢትየጵያ ንጉሥ በቲርሃቅ የሚመራ የግብጽ ሠራዊት እነርሱን ለመውጋት በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ሰናክሬም ሰማ፤ ወዲያውኑ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ በመልእክተኞች እጅ ላከ፡-
\s5
\v 10 «የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሆይ፣ የምትታመንበት አምላክ ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አትወድቅም ብሎ አያታልልህ፤
\v 11 የአሦር ነገሥታት አገሮችን ሁሉ እንዴት ፈጽመው እንደ ደመሰሱ ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
\s5
\v 12 የቀድሞ አባቶቼ የጎዛንን፣ የካራንና የሬጼፍን ከተሞች አጥፍተዋል፤ በተላሳር የሚኖሩትን የዓዴንን ሕዝብ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ከአማልክቶቻቸው አንድ እንኳ ሊያድናቸው ችሎአልን?
\v 13 ለመሆኑ የሐማት፣ የአርፋድ፣ የሴፈርዋይም፣ የሄናዕና የዒዋ ከተሞች ነገሥታት የት አሉ?»
\s5
\v 14 ንጉሥ ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞች ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ ቤተ መቅደስም ወስዶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው፡፡
\v 15 እንዲህ ሲልም ጸለየ፡- «የሠራዊት አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በኪሩቤል ላይ የተቀመጥህ፣ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ የዓለምንም መንግሥታት የምትመራ አንተ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህ አንተ ነህ፡፡
\s5
\v 16 አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ የደረሰብንን ነገር ሁሉ ተመልከት፣ አንተን ሕያው የሆነከውን አምላክ በመስደብ ሰናክሬም የተናገረውን የዛቻ ቃል ሁሉ አድምጥ፤
\v 17 እግዚአብሔር ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት ብዙ ሕዝቦችንና ምድራቸውን መደምሰሳቸው እርግጥ ነው፡፡
\v 18 ከእንጨትና ከድንጋይ ተጠርበው የተሠሩ የሰው እጅ ሥራ እንጂ አማልክት ስላልነበሩ በእሳት ላይ ጥለው አጠፉአቸው፡፡
\s5
\v 19 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፣ አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን የዓለም መንግሥታት ሁሉ ያውቁ ዘንድ አሁን ከአሦር ንጉሥ አድነን፡፡»
\s5
\v 20 ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፡- «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‹ስለ አሦር ንጉሠ ነገሥት ስለ ሰናክሬም ዛቻ ወደ እኔ የጸለይከውን ጸሎት ሰምቻለሁ፡፡
\v 21 ስለ እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፡- የጽዮን ድንግል ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ አንተ እየሸሸህ ሳለህ፣ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች ከኋላህ ሆነው ራሳቸውን ይነቀንቁብሃል፡፡
\v 22 የሰደብከውና የተዳፈርከው ማንን ነው? ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው በማን ላይ ነው? በትዕቢትስ ዐይንህን ያነሳኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡
\s5
\v 23 በመልእክተኞችህ አማካይነት፣ በእግዚአብሔር ላይ ስድብን አብዝተሃል፤ ‹በሠረገሎቼ ከፍተኛ ወደ ሆኑት ተራራዎች፣ ወደ ሊባኖስ ጫፍ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹን የሊባኖስ ዛፎችዋንና ምርጦቹን ዝግባ ቆርጬአለሁ፤ ወደ ዳርቻዋና ውብ ወደሆነው ጫካዋ ደርሼአለሁ፤› ብለሃል፡፡
\v 24 ‹በባዕድ አገር ጉድጓድ ቆፍሬ ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ኮቴዎች የግብጽን ወንዞች አድርቄአለሁ› ብለህ ታብየሃል፡፡
\s5
\v 25 ሰናክሬም ሆይ! አስተውል፤ ጥንቱኑ እኔ እንደ ወሰንኩት፣ በቀድሞው ዘመን እንዳቀድኩትና አሁን በሥራ ላይ ባዋልኩት መሠረት የተጠናከሩ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት እንድትለውጥ ያደረግኹህ እኔ መሆኔን አልሰማህምን?
\v 26 የእነዚያ አገር ነዋሪዎች ኃይላቸው ተዳክሞ፣ ተስፋ በመቁረጥ እንዲያፍሩ ተደርገው በምሥራቅ ነፋስ እንደተመቱ የመስክ አትክልቶች፣ እንደ ቀጨጩ አረንጓዴ ቡቃያዎች፣ በጣራ ላይ እንደበቀሉ ሣር ናቸው፡፡
\s5
\v 27 እኔ ግን መነሣትህንና መቀመጥህን፣ መውጣትህንና መግባትህን፣ እንዲሁም እኔን መቃወምህን ዐውቃለሁ፡፡
\v 28 በእኔ ላይ ያለው ተቃውሞህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአል፤ በአፍንጫህ ትናጋ፣ በአፍህም ልጓም አድርጌ፣ በመጣህበት መንገድ እመልስሃለሁ፡፡»
\s5
\v 29 ከዚያም ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን አንዲህ አለው፤ «ይህ ሁሉ እንደሚፈጸም ምልክቱ ይህ ነው፣ በአሁኑና በሚቀጥለው ዓመት ሳይዘሩት የሚበቅለውንና የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን የራሳችሁን እህል ዘርታችሁ ታመርታላችሁ፤ ወይንም ተክላችሁ ፍሬውን ትበላላችሁ፤
\v 30 በይሁዳ ከጥፋት የተረፉት ሁሉ ወደ መሬት ሥር ሰድዶ እንደሚያድግና እንደሚያፈራ ተክል ይሆናሉ፤
\v 31 ከኢየሩሳሌምና ከጽዮን ተራራ የተረፉት ወገኖች ይወጣሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ይፈጽማል፡፡»
\s5
\v 32 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን ንጉሠ ነገሥት የተናገረውም ቃል ይህ ነው፡- «ሰናክሬም ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባባትም፤ አንድ ፍላጻ እንኳ አይወረውርባትም፤ ጋሻ ያነገበ ወታደርም ወደ እርስዋ አይቀርብም፤ በአፈር ቁልልም አትከበብም፡፡
\v 33 እርሱ ወደዚህች ከተማ ሳይገባ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡
\v 34 ስለ ራሴ ክብርና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ይህችን ከተማ እኔ ራሴ ተከላክዬ አድናታለሁ፡፡»
\s5
\v 35 በዚያው ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አሦራውያን ሰፈር አልፎ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ በማግስቱ በማለዳ ሰዎች በሚነቁበት ጊዜ ሁሉም ሞተው ተገኙ፡፡
\v 36 ስለዚህ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ወደ ኋላው በማፈግፈግ ወደ ነነዌ ተመለሰ፡፡
\v 37 ከዕለታት በአንዱ ቀን ናሳራክ በሚል ስም በሚጠራው ባዕድ አምላኩ ቤተ መቅደስ ውስጥ በስግደት ላይ እንዳለ፣ ከልጆቹ ሁለቱ በተለይ አደራሜሌክና ሳራሳር ተብለው የሚጠሩት በሰይፍ ገደሉት፤ እነርሱም ወደ አራራት አምልጠው ሄዱ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ከልጆቹ አንዱ አስራዶን የተባለው ነገሠ፡፡
\s5
\c 20
\p
\v 1 በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፡፡ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጎበኘው ሄዶ፡- «እግዚአብሔር ‹ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ሁሉን ነገር አስተካክል› ብሎሃል» ሲል ነገረው፡፡
\v 2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፡-
\v 3 «እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፣ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!» እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡
\s5
\v 4 ኢሳይያስ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ የቤተ መንግሥቱን መካከለኛ አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፡-
\v 5 «ሕዝቤን ወደሚመራው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ተመልሰህ በመግባት እንዲህ በለው፡- ‹እኔ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም ተመልክቻለሁ፤ እኔ እፈውስሃለሁ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፡፡
\s5
\v 6 በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ በመታደግ አድናለሁ፡፡ ስለ ክብሬና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ከተማይቱን በመከላከል እጠብቃታለሁ፡፡”
\v 7 ስለዚህ ኢሳይያስ የንጉሡን አገልጋዮች «የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ አምጡልኝ» ብሎ አመጡለት፤ በቁስሉ ላይ ባደረጉለት ጊዜ የሕዝቅያስ ቁስል ተፈወሰ፡፡
\s5
\v 8 ንጉሥ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን «እግዚአብሔር እንደሚፈውሰኝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ እንደምችል በምን ምልክት ዐውቃለሁ?» ሲል ጠየቀው፡፡
\v 9 ኢሳይያስም «እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ ራሱ ምልክት ይሰጥሃል፤ እንግዲህ አሁን የምትመርጠው ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ነው? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?» ሲል ጠየቀው፡፡
\s5
\v 10 ሕዝቅያስም «ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ ይቀላል፤ ስለዚህ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርግልኝ» አለው፡፡
\v 11 ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ንጉሥ አካዝ ባሠራው ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ፡፡
\s5
\v 12 በዚያኑ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ መታመሙን ሰምቶ ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት፡፡
\v 13 ሕዝቅያስ መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ፣ ብሩንና ወርቁን፣ ቅመማ ቅመሙንና ሽቶውን፣ የጦር መሣሪያውንም ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ያላሳያቸው አንድም አልነበረም፡፡
\s5
\v 14 በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ፣ «እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?» ብሎ ጠየቀው፡፡ ሕዝቅያስም «እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው» ሲል መለሰለት፡፡
\v 15 ኢሳይያስም «በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ» ሲል ጠየቀው፡፡ ሕዝቅያስም «ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤቱ ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው አንድም ነገር የለም» አለ፡፡
\s5
\v 16 ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፡- «ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣
\v 17 ‹የቀድሞ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ድረስ ያከማቹት፣ በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርም።
\v 18 ከዘሮችህም አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡»
\s5
\v 19 ንጉሥ ሕዝቅያስም በተለይ በእርሱ ዘመን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለው ስለ ተረዳ «ከእግዚአብሔር ተልከህ የተናገርከኝ ቃል መልካም ነው» ሲል መለሰ፡፡
\v 20 ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራው ጭምር፣ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንዴት እንደ ሠራና ወደ ከተማይቱ ውሃ ለማምጣት ያስቆፈረው የመሬት ውስጥ ቦይ አሠራር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 21 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ፡፡
\s5
\c 21
\p
\v 1 ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሐፍሴባ ተብላ ትጠራ ነበረ፡፡
\v 2 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፡፡
\v 3 ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ አጥፍቶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች እንደገና እንዲሠሩ አደረገ፡፡ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ባደረገውም ዐይነት ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፣ አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስልን ሠራ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ፡፡
\s5
\v 4 እግዚአብሔር እንዲመለክበት ባዘዘው ስፍራ ማለትም በቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን አቆመ፡፡
\v 5 በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፡፡
\v 6 የገዛ ልጁንም መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት በመሥራቱ የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሣ፡፡
\s5
\v 7 በቤተ መቅደሱም ውስጥ የአሼራን ምስል አኖረ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን «ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እኔ ለዘለዓለም እንድመለክበት ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት ስፍራ ነው፡፡
\v 8 የእስራኤል ሕዝብ ትእዛዞቼን ቢጠብቁና ለአገልጋዬ ለሙሴ የሰጠሁትንም ሕግ ቢፈጽሙ፣ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ከዚህች ምድር ተነቃቅለው እንዲጠፉ አላደርግም» ሲል ነግሮአቸው የነበረው ነው፡፡
\v 9 የይሁዳ ሰዎች ግን ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ይልቁንም ምናሴ እስራኤላውያን ወደፊት እየገፉ ሲመጡ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋላቸው ሕዝቦች ይፈጽሙት ከነበረው ይበልጥ ወደ ክፉ ኃጢአት መራቸው፡፡
\s5
\v 10 ስለዚህ እግዚአብሔር በአገልገጋዮቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፡-
\v 11 «የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አሳፋሪ ነገር አደረገ፤ ይኸውም ቀድሞ ከነዓናውያን ይፈጽሙት ከነበረው ሁሉ የከፋ ነው፤ በሠራቸውም ጣዖቶች የይሁዳን ሕዝብ ወደ ኃጢአት መራ፡፡
\v 12 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የመጣው በጣም ከባድ መቅሰፍት ይህ ነው፤ ስለ እርሱም የሚሰማ ሰው ሁሉ በድንጋጤ ጆሮው ጭው ይላል፡፡
\s5
\v 13 ሰማርያንና የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ከነዘሮቹ እንደ ቀጣሁ ኢየሩሳሌምንም እቀጣለሁ፤ ሳሕን ከተወለወለ በኋላ ተደፍቶ እንደሚቀመጥ፣ እኔም ኢየሩሳሌምን ከኃጢአት አጸዳታለሁ፡፡
\v 14 ከጥፋት የተረፈውን ሕዝቤን ለጠላቶቹ ተላልፎ እንዲሰጥ እተወዋለሁ፤ እርሱም ይማረካል፤ ንብረቱም ይዘረፋል፡፡
\v 15 በእነርሱም ላይ ይህን ሁሉ የማደርግበት ምክንያት የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ኃጢአት ሠርተው እኔን በማሳዘናቸውና ቁጣዬን በማነሣሣታቸው ነው፡፡»
\s5
\v 16 ከዚህም በተጨማሪ ምናሴ የይሁዳን ሕዝብ ወደ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔርን ወደሚያሳዝን ኃጢአት ከመምራት አልፎ፣ ንጹሓን የሆኑትን ብዙ ሰዎችን በመፍጀት የኢየሩሳሌምን መንገዶች በደም እንዲጥለቀለቁ አድርጎአል፡፡
\v 17 ምናሴ ያደረገው ሌላው ነገርና የፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሓፍ ተመዝቦ ይገኛል፡፡
\v 18 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱ ግቢ «የዖዛ አትክልት ስፍራ» ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ፡፡
\s5
\v 19 አሞን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሜሶላም ተብላ የምትጠራ የዮጥባ ከተማ ተወላጅ የሐሩስ ልጅ ነበረች፡፡
\v 20 አሞን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፡፡
\s5
\v 21 የአባቱንም መጥፎ አርአያነት ሁሉ ተከተለ፤ አባቱ ይሰግድላቸውና ያመልካቸው የነበሩትንም ጣዖቶች ሁሉ አመለከ፡፡
\v 22 የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርንም ተወ፤ እግዚአብሔርንም አልተከተለም፡፡
\v 23 አገልጋዮቹ ባለሥልጣኖችም በአሞን ላይ አድመው በራሱ ቤት ውስጥ ገደሉት፡፡
\s5
\v 24 የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ደምስሰው ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ፡፡
\v 25 አሞን ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 26 አሞን «የዖዛ አትክልት ስፍራ» ተብሎ በሚጠራው መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ፡፡
\s5
\c 22
\p
\v 1 ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ይዲዳ ተብላ የምትጠራ የባሱሮት ከተማ ተወላጅ የሆነው የአዳያ ልጅ ነበረች፡፡
\v 2 ኢዮስያስ የቀድሞ አባቱን የዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፡፡ ወደ ግራም ቀኝም አላለም፡፡
\s5
\v 3 ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የሜሶላም የልጅ ልጅ፣ የኤዜልያስ ልጅ የሆነውን የቤተ መንግሥቱን ጸሓፊ ሳፋንን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት መልእክት ወደ ቤተ መቅደስ ላከው፡፡
\v 4 «ኬልቂያስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደህ፣ ወደ ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በር አጠገብ በየተራ ከሕዝቡ ገንዘብ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ካህናት እስከ አሁን ምን ያህል ገንዘብ ከሕዝቡ እንደሰበሰቡ የሚገልጥ የሒሳብ ማስረጃ ይዘህ እንድትመጣ አለው፡፡
\v 5 የመቅደሱን እድሳት ለመቆጣጠር ለተሾሙት ሰዎች ያስረክቡ፤ እነርሱም የተረከቡትን ገንዘብ ቤተ መቅደሱን ለሚጠግኑ፣ ለአናጢዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ይክፈሉ፡፡
\s5
\v 6 እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሳንቃዎችንና የተጠረቡ ድንጋዮችን ይግዙ፡፡
\v 7 ነገር ግን የሥራው ኃላፊዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ሆኑ እነርሱን ስለ ገንዘቡ አወጣጥ መቆጣጠር አያስፈልግም፡፡»
\s5
\v 8 ጸሐፊው ሳፋን ከንጉሡ የተላከውን ትእዛዝ ለኬልቂያስ ሰጠው፤ ኬልቂያስም «የሕጉን መጽሐፍ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገኘሁ» ብሎ ለሳፋን ሰጠው፤ ሳፋንም ተቀብሎ አነበበው፡፡
\v 9 ጸሐፊውም ሄደና «አገልጋዮችህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ተቀብለው ለእድሳቱ ሥራ ኃላፊዎች ለሆኑት ሰዎች አስረክበዋል» ሲል አስረዳ፡፡
\v 10 ከዚያም ጸሐፊው ሳፋን ለንጉሡ «ካህኑ ኬልቂያስ አግኝቶ የሰጠኝ መጽሐፍ» ነው አለው፡፡
\s5
\v 11 ንጉሡም፣ የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፡፡
\v 12 እርሱም ለካህኑ ለኬልቂያስ፣ የሳፋን ልጅ ለሆነው ለአኪቃም፣ የሚክያስ ልጅ ለሆነው ለዓክቦር፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሆነው ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፡፡
\v 13 «እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቆጥቶአል፡፡»
\s5
\v 14 ካህኑ ኬልቂያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦር፣ ሳፋንና ዓሳያ በኢየሩሳሌም አዲስ በተሠራው ሰፈር የምትኖረውን ሕልዳና ተብላ የምትጠራውን ነቢይቱን የሴሌም ሚስት ለመጠየቅ ሄዱ። የሐርሐስ የልጅ ልጅ የቲቅዋ ልጅ የሆነው የቤተ መቅደስ አልባሳት ኃላፊ ነበር፤ እነርሱም የሆነውን ሁሉ ለነቢይቱ አስረዱአት፡፡
\v 15 እርስዋም እንዲህ አለቻቸው፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፡- ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፡-
\v 16 «እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ ውስጥ በተጻፈው መሠረት በዚህች ቦታና በሕዝብዋ ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፡፡
\s5
\v 17 እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ በእጃቸው በሠሩአቸው ጣዖታት ሁሉ እኔን አስቆጥተውኛል፤ ቁጣዬም አይበርድም፡፡
\v 18 እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‹አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተህ፡-
\v 19 ይህችን ቦታና ሕዝብዋን የተረገሙና ባድማ እንደማደርግ የተናገርኩትን ቃል በሰማህ ጊዜ ልብህ ተነክቶ ራስህን በማዋረድህ፣ ልብስህን በመቅደድና በፊቴም በማልቀስህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ፡፡
\s5
\v 20 ከዚህም የተነሣ በኢየሩሳሌም ላይ የማመጣውን ቅጣት በዐይንህ ሳታየው እስከምትሞትበት ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህም አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ፡፡» ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ፡፡
\s5
\c 23
\p
\v 1 ስለዚህ ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎችን ሁሉ ጠርቶ ሰበሰባቸው፡፡
\v 2 እነርሱም ካህናት፣ ነቢያት፣ ሌሎችም ሰዎች ከታናሾች ጀምሮ እስከ ታላቆች ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ መጡ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፡፡
\s5
\v 3 ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና አሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ ስለዚህም በዚህ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ለመቆም ተስማሙ፡፡
\s5
\v 4 ንጉሡም ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን፣ ረዳቶቹ የሆኑትን ካህናትና የቤተ መቅደስ በር ዘብ የሚጠብቁ ተረኞችን ጠርቶ ለባዓልና አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ፣ እንዲሁም ለከዋክብት ማምለኪያ ያገለግሉ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ንጉሡም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ከኢየሩሳሌም ውጪ ባለው በቄድሮን ሸለቆ በእሳት አቃጥሎ ዐመዱን ወደ ቤቴል ወሰደው፡፡
\v 5 በይሁዳ ከተማዎችና በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ባሉት ስፍራዎች ሁሉ በየኮረብታው ላይ በነበሩት መሠዊያዎች መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ የይሁዳ ነገሥታት ሾመዋቸው የነበሩትን ካህናት ሁሉ ከሥራ አሰናበተ፤ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ፣ ለፕላኔቶች፤ ለፀሐይ፣ ለጨረቃ፣ ለፀሐይና ለሰማይ ከዋክብት ሁሉ መሥዋዕት በማቅረብ የሚያገለግሉ ካህናትን ሁሉ አስወገደ፡፡
\s5
\v 6 አሼራ ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ምስል ከቤተ መቅደስ ነቅሎ ከከተማይቱ በማውጣት ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ትቢያ እስኪሆንም አድቅቆ፣ በሕዝብ መቃብር ላይ በተነው፡፡
\v 7 ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉ ሴቶች አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ መጋረጃ የሚፈትሉበትን ክፍል ሁሉ አጸዳ፡፡
\s5
\v 8 በይሁዳ ከተሞችና በመላ አገሪቱ ከጌባ እስከ ቤርሳቤህ የነበሩትን ካህናት ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፡፡ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን መሠዊያዎች ሁሉ ርኩስ መሆናቸውን አወጀ፤ እንዲሁም የከተማይቱ ገዢ ኢያሱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ከዋናው ቅጥር በር በስተግራ በኩል ባሠራው ቅጥር በር አጠገብ የሚገኙትን መስገጃዎች አፈራረሰ፡፡
\v 9 የከፍታ ቦታ ካህናት በቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ለማገልገል ያልተፈቀደላቸው ቢሆንም በወንድሞቻቸው ዘንድ የነበረውን እርሾ ያልነካውን ሕብስት በሉ፡፡
\s5
\v 10 ንጉሥ ኢዮስያስ በሔኖም ሸለቆ የነበረውን «ቶፌት» ተብሎ የሚጠራውን የአሕዛብ ማምለኪያ ቦታ የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ከዚህም የተነሣ «ሞሌክ» ተብሎ ለሚጠራው አምላክ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንም እንዳይኖር ተከለከለ፡፡
\v 11 የይሁዳ ነገሥታት ለፀሐይ አምልኮ መድበዋቸው የነበሩትን ፈረሶች ሁሉ አስወገደ፡፡ ለዚሁ አምልኮ ያገለግሉ የነበሩትን ሠረገሎች አቃጠለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቀደም ሲል ታላቁ ባለሥልጣን ናታን ሜሌክ በሚኖርባቸው ክፍሎች አጠገብና በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቅጥር በር አጠገብ ይገኙ ነበር፡፡
\s5
\v 12 ንጉሥ አካዝ ባሠራቸው መኖሪያ ክፍሎች ጣራ ላይ በሚገኘው ቤተ መንግሥት የይሁዳ ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን መሠዊያዎችና በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ንጉሥ ምናሴ አሠርቶአቸው የነበሩትን መስገጃዎቸ ሁሉ ኢዮስያስ ደመሰሳቸው፤ መሠዊያዎቹን ሰባብሮ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ ጣላቸው፡፡
\v 13 ንጉሡም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኩሰት ተራራ በስተ ደቡብ አስታሮት ተብሎ ለሚጠራው ለአሞን አምላክ ንጉሥ ሰሎሞን አሠርቶአቸው የነበሩትን አስጸያፊ ምስሎች፣ የሲዶናውያንና የሞዓባውያን አስጸያፊ የሆኑ ጣዖታትን ሁሉ ደመሰሰ፡፡
\v 14 ንጉሥ ኢዮስያስ የድንጋይ አምዶችን ሁሉ ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውንም የሴት አምላክ ምስሎች ሰባብሮ ጣለ፡፡ እነርሱም ቆመውበት የነበረውን የድንጋይ ዐምዶች ሰባብሮ ስፍራውንም የሙታን አጥንት ሞላበት፡፡
\s5
\v 15 እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤቴል አሠርቶት የነበረውን የማምለኪያ ቦታ ኢዮስያስ አፈራርሶ ጣለው፤ መሠዊያውን ነቅሎ የተመሠረተበትን ድንጋይ ሁሉ ሰባብሮ በማድቀቅ እንደ ትቢያ አደረገው፤ የአሼራንም ምስል በእሳት አቃጠለ፡፡
\v 16 ከዚያም ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት፣ በኮረብቶች ላይ የተሠሩ መቃብሮች አየ፤ በእነዚያም መቃብሮች ውስጥ የነበረውን አፅም ሁሉ አስወጥቶ በመሠዊያው ላይ በእሳት አቃጠለው፡፡ በዚህም ዓይነት መሠዊያው የረከሰ መሆኑን አስገነዘበ፤ ኢዮስያስ ይህንን ሁሉ በማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት በተደረገ የአምልኮ በዓል ላይ ንጉሥ ኢዮርብዓም በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ ነቢዩ የተናገረው የትንቢት ቃል ተፈጸመ፡፡ ንጉሥ ኢዮስያስ ዙሪያውን ሲመለከት ይህንን የእግዚአብሔር ቃል ተናግሮ የነበረው ነቢይ የተቀበረበትን መካነ መቃብር የማን ነው ሲል ጠየቀ፡፡
\s5
\v 17 የቤቴል ሕዝብ ከይሁዳ መጥቶ በዚህ መሠዊያ ላይ ይህንን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጸምበት ተናግሮ የነበረው የነቢዩ መቃብር ነው ሲሉ መለሱለት፡፡
\v 18 ኢዮስያስም እንዳለ ይኑር፣ የእርሱ አፅም ከዚህ መንቀሳቀስ የለበትም ሲል መለሰ፡፡ ስለዚህም የእርሱም ሆነ የሰማርያው ነቢይ አፅሞች ከዚያ እንዲነሡ አልተደረገም፡፡
\s5
\v 19 ከዚያም ንጉሥ ኢዮስያስ በማንኛይቱም የእስራኤል ከተማ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትን የእግዚአብሔርን ቁጣ ለማነሣሣት ምክንያት የሆኑ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን ሁሉ አፈራረሰ፡፡ በቤቴል ያደረገውን ሁሉ በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ፈጸመ፡፡
\v 20 በእነዚያ መሠዊያዎች ላይ ያገለግሉ የነበሩትንም የአሕዛብ ካህናት ሁሉ አረዳቸው፡፡ በመሠዊያዎቹም ላይ አጥንቶቻቸውን አቃጠለ፡፡ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡
\s5
\v 21 ከዚያም ንጉሥ ኢዮስያስ በቃል ኪዳን መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር የፋሲካ በዓል ያከብሩ ዘንድ ሕዝቡን አዘዘ፡፡
\v 22 መሳፍንት የሕዝቡ ገዢዎች ከነበሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን በማናቸውም የእስራኤል ወይም የይሁዳ ነገሥታት አማካይነት ይህንን የመሰለ የፋሲካ በዓል ተከብሮ አያውቅም፡፡
\v 23 ነገር ግን ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የእግዘአብሔር ፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ተከበረ፡፡
\s5
\v 24 ሊቀ ካህናቱ ኬልቂያስ በቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈው ሕግ ሁሉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በማሰብ፣ ንጉሥ ኡዮስያስ ከኢየሩሳሌምና ከሌላውም የይሁዳ ከተማ ሁሉ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ሁሉ የቤተ ሰብ አማልክት ጣዖቶችንና ሌሎችም አረማዊ የአምልኮ መፈጸሚያ ዕቃዎችን ሁሉ አስወገደ፡፡
\v 25 ለኦሪት ሕግ በመታዘዝ በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ኃይሉ እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደ ንጉሥ ኢዮስያስ ያለ ከእርሱም በፊት ሆነ ከእርሱ በኋላ ከቶ አልነበረም፡፡
\s5
\v 26 ይሁን እንጂ ይህም ሁሉ ሆኖ ንጉሥ ምናሴ ባደረገው ክፉ ነገር ምክንያት በይሁዳ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቁጣ እስከ አሁን ድረስ ገና አልበረደም ነበር፡፡
\v 27 ስለዚህ እግዚብሔር እንዲህ አለ፡- በእስራኤል ላይ ያደረግኹትን ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ አደርጋለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ሕዝብ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኳትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራል ብዬ የነበረውንም ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፡፡
\s5
\v 28 ንጉሥ ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 29 በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ኒካዑ የተባለው የግብጽ ንጉሥ የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመርዳት ሠራዊቱን እየመራ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተጓዘ፡፡ ንጉሥ ኢዮስያስም መጊዶ ላይ የግብጽን ሠራዊት ለማገድ ጦርነት ገጥሞ በዚያ ውጊያ ላይ ተገደለ፡፡
\v 30 አገልጋዮቹም ባለሥልጣኖች ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው እዚያ በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፡፡ የይሁዳም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን መረጡ፣ በአባቱም ፈንታ አነገሡት፡፡
\s5
\v 31 ኢዮአክስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ገዛ፤ እናቱም አሚጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የሆነው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፡፡
\v 32 ኢዮአክስ የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡
\v 33 እርሱንም ኒካዑ ተብሎ የሚጠራው የግብጽ ንጉሥ ኢዮአክስ በኢየሩሳሌም እንዳይነግሥ በሐማት ምድር በምትገኘው በሪብላ አስሮ ይሁዳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ብር ሠላሳ አራት ኪሎ ወርቅ ግብር እንዲከፍል ባደረገው ጊዜ የኢዮአክስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ሆነ፡፡
\s5
\v 34 ንጉሥ ኒካዑ የኢዮአክስ ልጅ ኤልያቄም በአባቱ በኢዮስያስ ፈንታ ተተክቶ በይሁዳ እንዲነግሥ አደረገ፡፡ ስሙንም በመለወጥ ኢዮአቄም ብሎ ጠራው፡፡ ኢዮአክስ በንጉሥ ኒካዑ ተማርኮ ወደ ግብጽ ተወሰደ፤ በዚያም ሞተ፡፡
\v 35 ኢዮአቄም ለግብጽ ንጉሥ ለኒዑዑ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንደየችሎታቸው በሕዝቡ ላይ ግብር ጣለ፡፡
\s5
\v 36 ኢዮአቄም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ዘቢዳ ተብላ የምትጠራ የሩማ ከተማ ተወላጅ የሆነው የፈዳያ ልጅ ነበረች፡፡
\v 37 ኢዮአቄም የቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡
\s5
\c 24
\p
\v 1 በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይሁዳን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ከገበረለት በኋላ እንደገና አመፀ፡፡
\v 2 እግዚብሔር በአገልጋዮቹ በነቢያት አማካይነት ይሁዳን ስለ ማጥፋት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም ወራሪ ቡድኖች ባቢሎናውያንን፣ ሶርያውያንን፣ ሞአባውያንንና አሞናውያንን በኢዮአቄም ላይ አስነሣበት፡፡
\s5
\v 3 ይህም ሁሉ የሆነው ንጉሥ ምናሴ በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የይሁዳን ሕዝብ ከፊቱ ለማስወገድ እግዚብሔር ባዘዘው መሠረት ነው፡፡
\v 4 በተለይ ምናሴ የንጹሓንን ሰዎች ደም በማፍሰሱና ኢየሩሳሌምንም በንጹሓ ደም በመሙላቱ ምክንያት ይህ ሁሉ ሊፈጸም ችሎአል፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚብሔር ለምናሴ ምሕረት ሊያደርግለት አልፈቀደም፡፡
\s5
\v 5 ኢዮአቄም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
\v 6 ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፈንታ ልጁ ዮአኪን ነገሠ፡፡
\s5
\v 7 የባቢሎን ንጉሥ ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ግብጽ ሰሜናዊ ጠረፍ ድረስ የግብጽ ይዞታ የነበረውን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ስለ ነበረ፣ የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ ከዚያ በኋላ ከግብጽ ውጪ ዘመቻ አላደረጉም፡፡
\s5
\v 8 ዮአኪን በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ገዛ፡፡ እናቱም ኔስታ ተብላ የምትጠራው የኢየሩሳሌም ተወላጅ የሆነው የኤልናታን ልጅ ነበረች፡፡
\v 9 አባቱ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚብሔር ፊት ክፉ አደረገ፡፡
\s5
\v 10 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን አጠቃ፤ ከተማይቱንም ከበባት፡፡
\v 11 ሠራዊቱ ከብቦ በነበረበት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡
\v 12 የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ከእናቱ፣ ከልዑላን መሳፍንቱ፣ ከጦር አዛዦቹና ከባለሥልጣናቱ ጋር ወደ ባቢሎን ንጉሥ ተወሰዱ፡፡ የባቢሎን ንጉሥም በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማረከው፡፡
\s5
\v 13 ናቡከደነፆርም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት የነበረውን ሀብት ሁሉ ጠራርጎ ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡ ቀደም ሲል እግዚብሔር በተናገውም ቃል መሠረት ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚብሔር ቤተ መቅደስ አሠርቶት የነበረውን የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰባበረ፡፡
\v 14 ናቡከደነፆር የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ልዑላን፣ መሳፍንቱን ሁሉና ሌሎችንም ታላላቅ ሰዎች ጭምር በድምሩ ዐሥር ሺህ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፡፡ ከእርሱም ጋር የዕደ ጥበብ ዐዋቂዎችንና የብረት አንጣሪዎችን ሁሉ ወሰደ፤ በይሁዳ እንዲቀሩ ያደረገው የመጨረሻዎቹን ድኾች ብቻ ነበር፡፡
\s5
\v 15 ናቡከደነፆር ዮአኪንን አስሮ ከእናቱ፣ ከሚስቶቹ፣ ከአገልጋዮቹ፣ ከባለሥልጣኖቹና ከይሁዳ ታላላቅ ሰዎች ጋር በአንድነት ሰብስቦ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፡፡
\v 16 የባቢሎን ንጉሥ ሰባት ሺህ ለውጊያ ብቃት ያላቸው ወንዶችን እንዲሁም አንድ ሺህ ብረት ቀጥቃጮችንና ዕደ ጥበበኞችን ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡
\v 17 ናቡከደነፆርም በዮአኪን ምትክ ማታንያ ተብሎ የሚጠራውን የዮአኪንን አጎት በይሁዳ አነገሠው፤ ስሙንም በመለወጥ ሴዴቅያስ ብሎ ጠራው፡፡
\s5
\v 18 ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም አሚጣል ተብላ የምትጠራ የልብና ከተማ ተወላጅ የነበረው የኤርምያስ ልጅ ነበረች፡፡
\v 19 እርሱም አባቱ ኢዮአቄም ባደረገው ዓይነት በእግዚአብሔር ክፉ አደረገ፡፡
\v 20 እግዚብሔር ከፊቱ እስኪያስወግዳቸው ድረስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ተቆጥቶ ነበር፡፡ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ፡፡
\s5
\c 25
\p
\v 1 ናቡከደነፆር መላው ሠራዊቱን አስከትቶ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት፣ ዐሥረኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ከባቢሎን መጥቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ወታደሮቹ ከከተማይቱ ውጪ ሰፍረው ዙሪያውን የሚከብብ አጥር ሠሩ፡፡
\v 2 ከበባው እስከ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆየ፡፡
\v 3 ስለዚህም አራተኛው ወር በገባ በዘጠነኛው ቀን ራቡ በጣም ስለ ጸና ሕዝቡ የሚመገበው እንዳችም ምግብ አልነበረም፡፡
\s5
\v 4 ከዚያም የከተማይቱ ቅጥር ተጣሰ፤ የባቢሎን ወታደሮች ከተማይቱን ዙሪያውን ከበው በመያዝ ቢጠብቁም እንኳ የይሁዳ ንጉሥ ወታደሮች በሌሊት አምልጠው ወጡ፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ ከሚያስገባው መንገድ ተነሥተው ሁለቱን ቅጥሮች በሚያያይዘው የቅጥር በር በኩል በማለፍ ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ፡፡
\v 5 ነገር ግን የከላደውያን ሠራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ አሳደደው፡፡ ወታደሮቹም ጥለውት ሸሹ፡፡
\s5
\v 6 ሴዴቅያስ ተይዞ በሪብላ ከተማ ወደሚገኘው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ተወሰደ፡፡ በዚያም ፍርድ አስተላለፉበት፡፡
\v 7 ሴዴቅያስም ዐይኑ እያየ ልጆቹ በፊቱ ታረዱ፡፡ ከዚህም በኋላ ናቡከደነፆር የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ አሳወረው፤ እጆቹንም በነሐስ ሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፡፡
\s5
\v 8 ናቡከደነፃር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት፣ አምስተኛው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ናቡዘረዳን ተብሎ የሚጠራው የናቡከደነፆር የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡
\v 9 እርሱም ቤተ መቅደሱን፣ ቤተ መንግሥቱን፣ በከተማው የሚኖሩትን የታላላቅ ሰዎች ቤት፣ በከተማው ውስጥ የሚገኙትንም ሌሎች ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፡፡
\v 10 በክብር ዘቡ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ወታደሮች በሙሉ የኢየሩሳሌምን ዙሪያ አጥር ደመሰሱ፡፡
\s5
\v 11 ከዚህ በኋላ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ቀርተው የነበሩትንና ሌሎችን ሰዎች እንዲሁም ከድተው ወደ ባቢሎናውያን የተጠጉትን ሁሉ ምርኮ አድርጎ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፡፡
\v 12 ነገር ግን ምንም ሀብት የሌላቸውን የመጨረሻ ድኾች አትክልት ኮትኳቾችና መሬት አራሾች እንዲሆኑ በይሁዳ ምድር ትቶአቸው ሄደ፡፡
\s5
\v 13 ባቢሎናውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩትን የነሐስ አምዶች፣ ባለ መንኮራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠራውን ታላቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት፡፡
\v 14 እነርሱም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ መኮስተሪያዎችን፣ የዕጣን ማስቀመጫዎችንና ከነሐስ የተሠሩ የቤተ መቅደስ መገልገያ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰዱ፡፡
\v 15 ጽናዎችንና ዱካዎችን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ በመሆናቸው ወሰዱአቸው፡፡
\s5
\v 16 ንጉሥ ሰሎሞን ለቤተ መቅደስ ያሠራቸውን ሁለቱን አምዶች፣ ባለመንኮራኩር የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ታላቁን የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎቸ፣ በክብደታቸው ምክንያት ሊመዝኑአቸው አልቻሉም፡፡
\v 17 አንዱ አምድ ስምንት ሜትር ነበረው፤ ጉልላቱ ከነሐስ የተሠራ ነበር፤ የጉልላቱም ቁመት አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ በዙሪያውም ከነሐስ በተሠራ መረብ ላይ የሮማን ፍሬ ቅርጽ የመሰለ ባለፈርጥ ጌጥ ተሠርቶበት ነበር፡፡
\s5
\v 18 የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዘረዳን ሊቀ ካህናቱን ሠራያን በማዕርግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የቤተ መቅደስ ዘበኞች እስረኛ አደርጎ ወሰዳቸው፡፡
\v 19 ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነው አንድ ባለሥልጣን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ የነበሩትን አምስቱን የንጉሥ አማካሪዎች፣ የአገሩን ሕዝብ ለወታደርነት ይመለምል የነበረው መኮንንና ሌሎችንም ስልሳ ሰዎችን ወሰደ፡፡
\s5
\v 20 ከዚያም ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ በሐማት ግዛት በምትገኘው በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፡፡
\v 21 የባቢሎንም ንጉሥ በዚያ እነርሱን አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው፡፡ በዚህም ዐይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ፡፡
\s5
\v 22 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የሳፋን የልጅ ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ወደ ባቢሎን ተማርከው ሳይወሰዱ ለቀሩት ሰዎች ሁሉ ኃላፊ ይሆን ዘንድ የይሁዳ ገዢ አድርጎ ሾመው፡፡
\v 23 እጃቸውን ያልሰጡ የይሁዳ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን ገዢ አድርጎ እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ ወደ ምጽጳ መጥተው ከእርሱ ጋር ተገናኙ፤ እነዚህም የጦር መኮንኖች የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያ ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋ ከተማ ተወላጅ የሆነው የተንሑሜት ልጅ ሠራያና የማዕካ ተወላጅ የሆነው ያእዛንያ ነበሩ፡፡
\v 24 ጎዶልያስ እነርሱንና ወታደሮቻቸውን እንዲህ አላቸው፤ ከባቢሎናውያን ባለሥልጣኖች የተነሣ ምንም ዐይነት ፍርሃት ሊያድርባችሁ እንደማይገባ ቃል እገባላችኋለሁ፤ በዚህች ምድር ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁሉ ነገር ይቃናላችኋል፡፡
\s5
\v 25 ነገር ግን በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የነበረውና የኤሊሳማ የልጅ ልጅ የሆነው የናታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ምጽጳ ሄደ፤ በዚያም አደጋ ጥሎበት ጎዶልያስን ገደለው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተገኙትን አይሁዳውያንንና ባቢሎናውያንን ሁሉ ገደለ፡፡
\v 26 ከዚህም የተነሣ ባቢሎናውያንን ስለፈሩ እስራኤላውያን ሀብታሞችና ድኾች ከጦር ሠራዊት መኮንኖች ጋር በአንድነት ተነሥተው ወደ ግብጽ ሸሹ፡፡
\s5
\v 27 ዮርማሮዴቅ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ከእስራት በመፍታት ምሕረት አደረገለት፤ ይህም የሆነው ዮአኪን ተማርኮ በሄደ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር በሃያ ሰባተኛው ቀን ነበር፡፡
\s5
\v 28 ዮርማሮዴቅ ለዮአኪን መልካም ነገር አደረገለት፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩ ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ማዕረግ ሰጠው፡፡
\v 29 ስለዚህም ዮአኪን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማዕድ እንዲመገብ ተፈቀደለት፡፡
\v 30 እርሱም በኖረበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር ቀለብ ይሰጠው ነበር፡፡